Home » Articles » በአዕምሮ አይደለም

በአዕምሮ አይደለም

“የእግዚአብሔር ነገር በአዕምሮ አይደለም፣

“መንፈሳዊ ነገር በሞኝነት ነው፣

“በአዕምሮ አይደለም ዝም ብሎ በእምነት መቀበል እንጂ መመራመር አያስፈልግምޡእየተባለ ሲነገር እንሰማለን፡፡

እንደሚታወቀው የአዕምሮ መሰረታዊ ተግባር መረጃ መቀበል፣ ማቀናጀት፣ ማመዛዘንንና ውሳኔ መስጠት ነው፡፡ በሕያውነት ለመቀጠል ከተፈለገ አዕምሮአችን እነዚህን ተግባራት  በስርዓት ማከናወን ይኖርበታል፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንዶች እምነት፣ በተለይም  መንፈሳዊ እምነት፣ አዕምሮን እንደማያሳትፍ እና ለእምነት አስፈላጊው ነገር በአዕምሮ አለመሆን እንደሆነ ሲናገሩ ያጋጥማል፡፡

 

እውነት እምነትን ከአዕምሮ ነጥሎ ማሰብ ይቻላልን? መጽሐፍ ቅዱስ እምነት ከመስማት እንደሆነ ይነግረናል፡፡ በመስማት ብቻ ግን እምነት ሊፈጠር እደማይችል እሙን ነው፡፡ ወደ እምነት ደረጃ ለመድረስ የሰማነውን ማመዛዘንና መወሰን አለብን፡፡ ይህ ደግሞ የአዕሮ ተግባር ነው፡፡ ያመንነው እግዚአብሔር ለአዕምሮአችን የእውነትን ብርሃን  ስላበራለት እንጂ አንዳንዶች እንደሚያስቡት እንዳይሰራ ስላደረገው አይደለም፡፡ የእግዚአብሔርን የክብሩን እውቀት ብርሃን እንዲሰጥ በልባችን ውስጥ የበራ፦ በጨለማ ብርሃን ይብራ ያለ እግዚአብሔር ነውና።እንዲል ቃሉ (2ቆሮ 4፡6)

 

መንፈሳዊነት  አዕምሮን  ከመሰረታዊው  የፍጥረት  ዓላማው  ማፋታት  አይደለም፡፡  መንፈሳዊ  ሰው  ማለትም  አዕምሮው  ለሰማያዊ መገለጥ ተገዢ ያደረገ ሰው ማለት እንጂ አዕምሮውን የማይጠቀም ማለት አይደለም፡፡ እምነት የአዕምሮና የፈቃድ የጋራ እንቅስቃሴ ነውና1፡፡ ፀረ-አለማመን መሆን ይቻላል፤ ፀረ-አዕምሮ መሆን ትርጉም የለሽ ነው፡፡

 

ጆናታን ኤድዋርድስ፣ ሰዎች  ምክንያታዊ አዕምሮ ያላቸው  በመሆናቸው ልባቸውን   ማግኘት የሚቻለው የእውነትን ብርሃን ለአዕምሮአቸው ማብራት ሲቻል ብቻ እንደሆነ ጽኑ እምነት እንደነበረው ይነገርለታል፡፡ የሰባኪው ስራ ሰሚዎቹ ምክንያታዊ የሆነ ጽኑ እምነት (reas onable pers uas ion or conviction) እንዲኖራቸው ማድረግ በመሆኑ ޠየእውነትን አብርሆት ለአዕምሮ በመስጠት ልብን ማቀጣጠል(ማግኘት)ያስፈልጋል2” (“enlighten the mind and inflame the heart”) ይል ነበር፡፡

 

በተመሳሳይ መልኩ ጥቅም ላይ የሚውለው የእግዚአብሔር ነገር በሞኝነት ነውየሚለውም አባባል ቢሆን ለአባባሉ እንደ መነሻ የሆነውን  የመጽሐፍ  ቅዱስ  ክፍል  በጥልቀት   ካለማጥናት  የመነጨ  ነው፡፡  ጳውሎስ  ለቆሮንቶስ  ሰዎች  በስብከት  ሞኝነት የሚያምኑትን ሊያድን የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ሆኗልና (ቆሮ 1፡21) ሲል የተናገረው ንግግር ነው መነሻ በማድረግ ብዙዎች ይህን ክፍል ጠቅሰው መንፈሳዊነት በሞኝነት እንደሆነ ለማስረዳት ይሞክራሉ፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ክፍሉን በጥንቃቄ ካለማንበብ የሚሰጥ ድምዳሜ ነው፡፡ በዚህ ክፍል የመስቀሉ ቃል፤ ማለትም ስለ ክርስቶስ የመስቀል ሞትና የደህንነት እውቀት የሚሰበከው ስብከት ሞኝነት እነደሆነ የተጠቀሰው ለሚጠፉት ነው፡፡ (1፡18)  ለእኛ ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነው፡፡ ወንጌል ለማዳን የሆነ የእግዚአብሔር ኃይል እና ምጡቅ መለኮታዊ ጥበብ እንጂ አረማውያን እንደቆጠሩት ተራ ተረት አይደለም፡፡

 

በክፍሉ ጥበበኞች ተብለው የተጠሩት (ቁ.20) የአህዛብ ፈላስፎች በተለይም የግሪክ ፍልስፍና የቀመሱ ሰዎች ናቸው፡፡3(አንዳንዶች የአይሁድ  መምህራንንም  ሊጨምር   ይችላል ይላሉ) ሐዋሪያው ጳውሎስ ታዲያ፣ እነርሱ እንደ ሞኝነት የቆጠሩት ስብከት “የእግዚአብሔር ጥበብ እንደሆነ እና (እግዚአብሔርን ለማወቅ የማያስችላቸው) የእነርሱ ጥበብ ግን ሞኝነት እንደሆነ ተናግሯል፡፡

 

“ጠቢብ የታለ? ሊቅስ የታለ? የዘመኑስ ፈላስፋ የታለ? እግዚአብሔር  የዓለምን ጥበብ  ሞኝነት አላደረገምን?  (ቁ.20)“..ይህም ለአይሁድ ማሰናከያ ለአህዛብም ሞኝነት ነው ለተጠሩት ግንިየእግዚአብሔር ኃይልና የእግዚአብሔር ጥበብ የሆነው ክርስቶስ ነው፡፡ (ቁ.23-24)  የማያምን  ሰው  እምነቴን  እንደ  ሞኝነት  ሊቆጥረው  ይችል  ይሆናል  እንጂ  የእኔ  እምነት  ሞኝነት  ሊሆን  አይችልም፡፡ ይልቁንም ጥበብ ነው፡፡ ይህም ጥበብ  እግዚአብሔር  አስቀድሞ ከዘመናት በፊት ለክብራችን የወሰነውިአይን ያላየችው፣ ጆሮም ያልሰማው፣ በሰውም ልብ ያልታሰበው፣ እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው ጥበብ ነው፡፡ (1ቆሮ 2፡7-9)

 

ርግጥ ነው፤ አንዳንዶች መንፈሳዊው ነገር በአዕምሮ አይደለም፤ ሲሉ በአመክንዮ  አይደረስበትም ለማለት  ፈልገው  ሊሆን እንደሚችል ይገባናል፡፡ ይሁን እንጂ ይህም  ቢሆን ሚዛናዊ ድምዳሜ አይመስልም፡፡ የምናምነው፣ አዕምሮ የፈቃድ እጁን ሲሰጥ ነው፡፡ ይህም በአመክንዮ እገዛ ጭምር የሚሆን ነው፡፡ ለዚህ የቤሪያ ሰዎች ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ “እነዚህ በተሰሎንቄ ከሚኖሩት ይልቅ ልበ ሰፊዎች ነበሩና፣ ነገሩ እንደዚሁ ይሆንን; ብለው ዕለት ዕለት መጽሐፍትን እየመረመሩ ቃሉን በሙሉ ፈቃድ ተቀበሉ (ሐዋ 17፡11)  ይህ  (የቤሪያ  ሰዎች  ምሳሌ)  እምነት እውነትን ለማስረዳት አመክንዮአዊ  ጥያቄዎችንና  ሙግቶችን በሚገባ ሊጠቀም እንደሚችል ጠቋሚ ነው፡፡ ሲ.ኤስ ሉዊስ እንዳለው እምነት ማለት እራሱ አመክንዮአችን  አንዴ ልክ ብሎ የተቀበላቸውን ነገሮች የሙጥኝ ብሎ የመያዝ ጥበብ ነውና4፡፡

 

“ዝም ብለህ እመን የሚለው አባባል ክርስትና እምነቱን ማስረዳት የማይችል ደካማና ፈሪ ኃይማኖት እንደሆነ እንዲታሰብ ያደርጋል፡፡ ጆን ካልቪን እምነቱን ለማስረዳትም ሆነ  ለመከላከል አመክንዮአዊ ክርክር መግጠም ቢኖርበት ወደ ኋላ እንደማይል ተናግሯል፡፡ “በራሴ በኩል ታላቅ ክህሎት ወይም አንደበተ ርቱዕነት ባልጎናጸፍም እንኳ፣ እግዚአብሔርን የሚንቁትን፣ የቅዱሳን መጽሐፍትን ስልጣን በብልጠታቸውና በቀልዳቸው ሊያብጠለጥሉ የሚፈልጉትን ሰዎች ክርክር መግጠም ካለብኝ፤ ልቅ አፋቸውን በቀላሉ ጸጥ ለማሰኘት ወኔው አለኝ፡፡5 ብሏል፡፡

 

ክርስትና ከመሰረቱም ቢሆን የአዕምሮ ጡንቻዎችን ከሚያንቀሳቅሱ ሙግቶች ነጻ አይደለም፡፡ የሐዋሪያው ጳውሎስ ተሞክሮ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ ޠበየሰንበቱ  ከአይሁድና ከግሪክ ሰዎች ጋር በምኩራብ ውስጥ እየተነጋገረ ሊያሳምናቸው ይጥር  ነበር፡፡ (ሐዋ 18፡28) ሐዋሪያው ጴጥሮስም ቢሆን ޠበእናንተ ስላለ ተስፋ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቋችሁ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፡፡ (ጴጥ. 3፡15) ሲል የእውነትን እውቀት ለመግለጽም ሆነ እምነትን ለመከላከል ሙግችን መጋፈጥ እንደሚኖርብን ይናገራል፡፡

 

አንዳንዶች አመክንዮ ብቻውን ልዕለ-ተፈጥሮአዊ የሆኑ የእግዚአብሔርን ተአምራቶች እንዴት ሊረዳ እና ሊያስረዳ ይችላል?” ብለው ይጠይቃሉ፡፡ በርግጥ ውስን ለሆነው ሰዋዊ አመክንዮ በእምነት ያረጋገጥናቸውን ነገሮች ሁሉ መርምሮ እንዲረዳ መተው አንችልም፡፡ ለምሳሌ አንዲት ሴት የመውለጃ እድሜዋ ካለፈ በኋላ ልትወልድ እንደማትችል   አመክንዮአችን  ይነግረናል፡፡  ያረጡ  ሴቶች ስለመውለዳቸው የሚናገረውን የመጽሐፍ ምንባብ የእምነት ድጋፍ በሌለው ሌጣ አመክንዮ ብቻ ልንረዳ እንደማንችል እሙን ነው፡፡ የዚህን ጊዜ በሚታየው ላይ የተመሰረተው ተፈጥሯዊ አመክንዮ በማይታየው ላይ  ለተመሰረተው (የእግዚአብሔርን ሁሉን ቻይነት ለሚያምነው)  አመክንዮ  መገዛት  ይኖርበታል፡፡ ይህም ޠየእምነት እና አመክንዮ ጥምረትޡክርስቲያናዊ አመክንዮን  ይፈጥራል፡፡ ጥምረቱም በሚታይ ማስረጃ የምንገነዘበው በእምነት ለምንገነዘበው  ሲገዛ የሚፈጠር ነው፡፡ ይህን አይነቱን አመክንዮ ምሁራን “ዳግም የተወለደ አመክንዮޡእያሉ ይጠሩታል፡፡

 

አመክንዮን ለእምነት በማስገዛት መጠቀም እየተቻለ በደፈናው መቃወም ትልቅ ስህተት ውስጥ የሚከት ነው፡፡ ቅዱስ አውጊስኖስን ሲናገር፤

“እግዚአብሔር ራሱ ከሌሎች ፍጥረታት አስበልጦ የሠራልንን በእኛ ውስጥ ያለውን  ያን የአመክንዮን ክፍል መጥላትን ይከለክላል፡፡ ስለዚህ  ለምናምንበት ነገር   ምክንያት ሳንቀበል ወይም ሳንፈልግ ለማመን እምበተኞች መሆን ይገባናል፡፡አመክንዮአዊ ነፍስ ባይኖረን ኖሮ ፈጽሞ ማመን አይቻለንም6  ብሏል፡፡

 

እምነት እንደ ኩሬ ውሃ የረጋ እና የማይንቀሳቀስ ነገር አይደለም፡፡ ቶማስ አኪውናስ “እምነት ማለት ሁል ጊዜ መመርመር፣ የበለጠ ለማወቅ መፈለግና የነገሮችን ግኑኝነት ማጤን እንጂ አዕምሮን ስራ-ፈት ማድረግ አይደለምޡ7ብሏል፡፡ ޠይልቁንም ካመንንበት ቅጽበት ጀምሮ ዛሬ በድንግዝገዝ የሚታየው በፍጹምነት መታየት እስከሚጀምርበት ጊዜ ድረስ አዕምሮአችን ይበልጥ የሚንቀሳቀስና የሚሰራ መሆን አለበት፡፡8” (1ቆሮ. 13፡12-13)

 

ጎትፍሬድ ኦሴ ሜንሳህ የተባሉ የነገረ መለኮት ምሁር፣ ޠየአዕምሮ ጡንቻዎችን  የማኮላሸት እምነትޡሲሉ ከጠሩት አጉል እምነት መጠንቀቅ እንደሚገባ ይናገራሉ፡፡

“ዛሬም  በእግዚአብሔር  ሕዝብ  መካከል  ጸረ-  ምሁር  አዝማሚያ  አለ፡፡እግዚአብሔር  አምላካችንን  በፍጹም  ሃሳባችን እንድንወድ ታዘናል፡፡ ሆኖም አንዳንድ ሰዎች ክርስትና በአብዛኛው ወደ ስሜት ክልል ያዘነብላል ብለው ስለሚያስቡ፣ ብዙ ማሰብ ከጀመርን ከእምነታችን እናፈነግጣለን ይላሉ፡፡ ከዚህ የጸረ-ምሁራን ወጥመድ እንዳትወድቁ ተጠንቀቁ፡፡9”

 

በጣም  የሚገርመው  ነገር፣  አንዳንድ  ክርስቲያኖች  በይዘቱ  መንፈሳዊ  ያልሆነውን  እውቀት  ብቻ  ሳይሆን  መንፈሳዊውን  እውቀት የሚመረምሩትንም ጭምር ያወግዛሉ፡፡ ቃሉን በጥልቀት የሚያጠኑትን ޠቃል ብቻውን ያደርቅሃል፤ ብዙ ጠልቀህ አትመራመርޡይላሉ፡፡ ይህ ሲያዩት መንፈሳዊ የሚመስል የአለማወቅ እምነት ነው፡፡ በመንፈስ ቅዱስ አስተማሪነት ላይ ብቻ ይደገፉ እንጂ መንፈሳዊ ነገሮችን የሚመረምሩ ሲገኙ ޠጎሽ አበጃችሁޡነው መባል ያለባቸው፡፡ መንፈሱ ޠየጥበብና የመገለጥ መንፈስޡነው፡፡ (ኤፌ 1፡17) በእርሱ እገዛ ቃሉን የሚያጠናን ልብ በጥበብና በአብርሆተ-መለኮት ይሞላል!

 

ለመሆኑ ሁሉንም ነገር ሳይጠይቁ መቀበል መንፈሳዊነት፣ መጠየቅ ደግሞ ስጋዊነት  እንደሆነ የሚነግሩን ሰዎችስ የሚናገሩትን ያውቁታል? ድንግል ማሪያም በድንግልና መሲህ እንደምትወልድ መልአኩ ባበሰራት ጊዜ፣ ከተፈጥሮ ሕግ የወጣ ነገር እንደተነገራት ስታውቅ ޠቃሉ የእግዚአብሔር እስከሆነ ድረስ አዕምሮ-ወለድ ጥያቄ  እንደምን ይጠየቃል?” ብላ ዝም አለችን?… “ወንድ ሳላውቅ (በድንግልና) ልጅ እንዴት  መውለድ እችላለሁ?” ስትል መጠየቅዋስ ޠምን አይነት የማታምን፣ ስጋዊና የአዕምሮ ብቻ  ሰው ናት?” ያስብላታልን?   መልአኩ   በመጠየቋ  ሲወቅሳት  አናይም፡፡  ለአዕምሮዋ   ጥያቄ   አዕምሮን  የሚያሳምን  መልስ  ሰጣት  እንጂ፡፡ “ለእግዚአብሔር የሚሳነው ምንም ነገር  የለምޡሲል፡፡ ከዚህ በኋላ ነው ማሪያም ޠአሜን..እንደ ቃልህ ይሁንልኝޡያለችው፡፡  ታዲያ እኛስ አትጠይቁ አዕምሯችሁን አፍናችሁ፣ አሜን ብቻ በሉ የምንባለው ለምንድነው?፡:

 

ኃይማኖተኞች ጥያቄን አብዝተው ይፈራሉ፡፡ የሚፈሩትም በቂ መልስ የለኝም ብለው ስለሚያስቡ ሊሆን ይችላል፡፡ መፍትሔው ታዲያ ለመልስ መዘጋጀት እንጂ እንደ ሰነፍ  መምህር ጥያቄን ማፈን አይደለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ መጠየቅን እጅግ የሚያበረታታ  መጽሐፍ ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ ያስተማራቸው አብዛኞቹ ትምህርቶች ደቀመዛሙርቱ በጠየቋቸው ጥያቄዎች ላይ ተመስርቶ ያስተማራቸው ናቸው፡፡ መንፈሳዊ ሚስጥራትን መመርመርިመጠየቅިማወቅና ለሚጠይቁን ሁሉ መልስ ለመስጠት የተዘጋጀን መሆን ይጠበቅብናል፡፡

 

ብዙ ጊዜ መንፈሳዊ ነገሮች በሞኝነት መደረግ እንዳለባቸው አዘውትረው የሚናገሩ  ሰዎች ግላዊ ޠልምምዶቻቸውንޡያለ ፍተሻ በሕዝቡ ላይ መጫን የሚፈልጉ ናቸው፡፡ ይህም  አካሄድ በርካታ ካሪዝማዊ ቀውሶች እንዳስከተለ ይታወቃል፡፡ ቀደም ሲል በአገረ አሜሪካ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ በምዕራቡ የአፍሪካ ክፍል ባሉ ቤተክርስቲያናት ጆሮን ጭው የሚደርጉ ልምዶችን መስማት የተለመደ ነው፡፡ የእግዚአብሔርን መንጋ በመንፈሳዊ ልምምድ ሰበብ ሳር የሚያስግጡ፣ ቤንዚን የሚያጠጡ፣ እባብ የሚያስውጡ እና መርዝ አጠጥቶ እስከመግደል የደረሱ መጋቢዎች አሉ፡፡ እነዚህን ነገሮች ሲያስደርጉም ሕዝቡን መንፈሳዊ ነገር ስለሆነ በሞኝነት እንዲያደርገው በማዘዝ ነው፡፡ የታዘዙአቸው ምዕመናን ግን እንዳላተረፉ ታይቷል፡፡

 

መጽሐፍ ይህን ይለናል፤

የጌታ ፈቃድ ምን እንደ ሆነ አስተውሉ እንጂ ሞኞች አትሁኑ። (ኤፌ. 5፡17)

ወንድሞች ሆይ፥ በአእምሮ ሕፃናት አትሁኑ፤ ለክፋት ነገር ሕፃናት ሁኑ እንጂ በአእምሮ የበሰሉ ሁኑ። (1ቆሮ)

እያሰብን እንመን፤ እያመንን እናስብ

(ቅዱስ አውግስጢኖስ)

  1. ሮናልድ ደን (ተርጓሚ ጳውሎስ ፈቃዱ)፣ የእምነት ኃይል፤ ገጽ.14
  2. The S upremacy of God in preaching, J ohn Piper (US A, Baker Book Hous e, Grand Rapids , 1996) 85
  3. New International Vers ion (NIV) S tudy Bible፡  Fully revis ed (US A, Michigan: Grand Rapids , 2002) 1777
  4.  ሲ. ኤስ. ሉዊስ፤ ክርስትና ለጠያቂ አዕምሮ (ተርጓሚ አዲስ አሰፋ)፣ ገጽ 125
  5. ምህረቱ ጴ. ጉታ፤ እምነትና አመክንዮ የተጣመሩ ወይስ የተፋቱ፡ እያመንን እናስብ፤ እያሰብን እንመን (አዲስ አበባ፣ ኤስ አይ ኤም ስነ ጽሑፍ ክፍል፣ የካቲት 2008 ዓ.ም) 45
  6. ዝኒ ከማሁ ፣ 28
  7. Eugene T. S elle, Thomas Aquinas : Faith and reas on, (Graded Pres s , 1988) 23
  8. ዝኒ ከማሁ 23
  9. ጎትፍሬድ ኦሴ- ሜንሳህ (ትርጉም ሚናስ ብሩክ) ፤ ይፈለጋሉ፡ አገልጋይ መሪዎች፣ ስነ መለኮታዊ እይታ በአፍሪካ ቁ. 3 (S IM Publis hing, የህትመት ዘመን አልተገለጸም) 33

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

x

Check Also

Fikadu Borena Week Four

Related

%d bloggers like this: