Home » Articles » በቤተክርስቲያን ውስጥ ችላ እየተባሉ የመጡ የጋራ ኃጢአቶች!

በቤተክርስቲያን ውስጥ ችላ እየተባሉ የመጡ የጋራ ኃጢአቶች!

በቤተክርስቲያን ውስጥ ችላ እየተባሉ የመጡ የጋራ ኃጢአቶች!

አሉላ ጌታሁን

 

፩ – የሀሰት ምሥክርነት

ሁላችንም “ኃጢአተኞችነን ነን”፤ መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ በዚህ ጉዳይ በጣም ግልጽ ነው (1ኛ ዮሐንስ 1፥8-10)። ይህ ማለት ግን፤ ኃጢአተኞች ሆነን የመቀጠልን ነፃነት አለን ማለት አይደለም! ነገር ቀላል አርገን የምናያቸው ኃጢአቶች እንዳሉ ግልፅ ነው። ከነዚህም ውስጥ አንዱ የሀሰት ምሥክርነት ነው። በምንም አንይነት ሁኔታ በሌሎች ላይ የሐሰት ምስክር መሆን አይገባንም። እውነቱን “ልንለጥጠው” እንችላለን፥ ነገር ግን ግማሽ እውነት፤ ውሸት ነው።

እኔ በበኩሌ ይህን ተላልፌ አውቃለሁ፥ እናንተም እንደኔው ይህን ትዕዛዝ ተላልፋቹ ታቃላቹ ብዬ አስባለሁ። ውሸቴ ተይዞብኛ ያቃል፤ እኔም ሌሎችን በውሸታቸው ይዤ አውቃለው። አብዛኛዎቹ እውነተኛ ክርስትያኖች በዚህ ጉዳይ ንስሓ ገብተው ይቅርታ እንደሚጠይቁ ሁሉ፣ “ክርስቲያን ነኝ” እያሉ በውሸታቸው ተደላድለው የሚኖሩም አሉ። ነገር ግን ይህ በፍፁም ሊሆን አይገባም ምክንያቱም እግዚአብሔር ከሚጠላቸውና ሞትንም ከሚያስከትሉ ሰባት ኃጢአቶች አንዱ የሀሰት ምሥክርነት ነውና ይሄም ደግሞ “በሐሰት የሚናገር ሐሰተኛ ምስክር” (መጽሐፈ ምሳሌ 6፥19) እና “ሐሰተኛ ምላስ” (መጽሐፈ ምሳሌ 6፥17) ያካተተ ነው።

 

፪ – ሐሜት

ሐሜት ተራ የሚመስል ግን እግዚአብሔር በጣም የሚጠላው ኃጢአት ነው። ሐሜት የሰዎችን ጓደኝነትን እና የወዳጅነት ግንኙነቶችን ይከፋፍላል እንዲሁም ያጠፋል። ስለ እግዚአብሔር እንደተነገረው “እግዚአብሔር የሚጠላቸው ስድስት ነገሮች ናቸው፥ ሰባትንም ነፍሱ አጥብቃ ትጸየፈዋለች፤” (መጽሐፈ ምሳሌ 6፥16)፤ በመቀጠልም “በሐሰት የሚናገር ሐሰተኛ ምስክር በወንድማማች መካከልም ጠብን የሚዘራ።” (መጽሐፈ ምሳሌ 6፥19) ይላል። እግዚአብሔር በቤተክርስቲያን ውስጥ የሚፈጥረውን አንድነት እና ህብረት፤ ይኸው ሐሜት የማጥፋት አቅም አለው።

ይሄ ጉዳይ ታዲያ በቆሮንጦስ ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ ትልቅ ችግር እንደነበር ጳውሎስ “ሁላችሁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ በአንድ ልብና በአንድ አሳብም የተባበራችሁ እንድትሆኑ እንጂ መለያየት በመካከላችሁ እንዳይሆን…” በማለት ጽፏል (1 ቆሮ 1፥10) ምክንያቱ ሐሜት የቅርብ ጓደኝነትን ይለያልና፤ “ጠማማ ሰው ጥልን ይዘራል፤ ጆሮ ጠቢ ሰው የተማመኑትን ወዳጆች ይለያያል።” (መጽሐፈ ምሳሌ 16፥28)

 

፫ – ስርቆት

ምናልባት ባንኮችን ላንዘርፍ እንችላለን (ወይ ደግሞ በቅርብ ቀን ተያዙ እንደተባሉት የመንግስት ባለስልጣናት እና ባለሃብቶች ብዙ ገንዘብ ላንሰርቅ እንችላለን)፤ ነገር ግን ትንሽ በሚመስሉ ነገሮች እራሳችንን በስርቆት ልንይዝ እንችላለል። ለምሳሌ ያህል የሥራ ገበታችንን በሰዓት ስርቆት ልንበድል እንችላለን፣ ሆን ብለን ከነገሮቹ ትንሽነት የተነሳ፤ ካለባለቤቱ ፈቃድ እስክሪብቶችን፣ ወረቀቶችን፣ እና አልፎ አልፎ ደግሞ ትንሽ ከበድ ያሉ ነገሮችን ልንሰርቅ እንችላለን። በስራ ቦታ እንኳን እየቻልን መስጠት ያለብንን ካልሰጠን እና ካልሰራን፤ እኛን “ተገቢ ስራቸውን እየሰሩ ነው” ብለው እየከፈሉ ከሚያሰሩን ሰዎች እየሰረቅን ነው።

ጳውሎስ ለንብረት እና ለሰዓት ዘራፊዎች በጽሑፉ እንዲህ ሲል አስጠንቅቋል፤ “የሰረቀ ከእንግዲህ ወዲህ አይስረቅ፥ ነገር ግን በዚያ ፈንታ ለጎደለው የሚያካፍለው እንዲኖርለት በገዛ እጆቹ መልካምን እየሠራ ይድከም።” (ኤፌሶን 4፥28)

በሮሜ የነበረውችውን ቤተክርስቲያን ደግሞ “እንግዲህ አንተ ሌላውን የምታስተምር ራስህን አታስተምርምን? አትስረቅ ብለህ የምትሰብክ ትሰርቃለህን?” (ሮሜ 2 21) በማለት ገስጿል።

 

፬ – መመኘት/መጎምጀት

ምኞት/መጎምጀት፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተዘረዘረው አሥርቱ ትዕዛዛት ውስጥ ብዙዎቻችን በትኩረት ልናየው እና ልናስተውለው ያልቻልነው ኃጢአት ነው። የባልንጀራን ባል/ሚስት መመኘት፣ ሃብትና ንብረትን መመኘት፥ እንዲሁም ዝናን እና እውቅናን መመኘትን መጥቀስ እንችላለን።

መጎምጀት/መመኘት ጳውሎስን ካስቸገሩት ችግሮች ውስጥ አንዱ እንደሆነ ተናግሯል። እራሱ እንደፃፈው፦ “እንግዲህ ምን እንላለን? ሕግ ኃጢአት ነውን? አይደለም፤ ነገር ግን በሕግ ባይሆን ኃጢአትን ባላወቅሁም ነበር፤ ሕጉ። አትመኝ ባላለ ምኞትን ባላወቅሁም ነበርና። [8] ኃጢአት ግን ምክንያት አግኝቶ ምኞትን ሁሉ በትእዛዝ ሠራብኝ፤ ኃጢአት ያለ ሕግ ምውት ነውና። (ሮሜ 7፥7-8)

በምትመኝበት/በምንጎመጅበት ወቅት፤ እግዚአብሔርን “እግዚአብሔር ሆይ፤ በሰጠኸኝ እና ባለኝ ነገር አልረካሁም – ከዚህ በላይ እፈልጋለሁ!” እያልነው እንደሆን እናስተውል።

 

፭ – ወላጆችን አለማክበር

እዚች ላይ ብዙ ብቆይ አልያም ደግሞ ለብዛው ሰፋ ያለ ነገር ብፅፍ ደስ ይለኝ ነበር። በተለይ ዛሬ ከምናያቸው ነገሮች የተነሳ በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ሰዎች ከማዘናቸው የተነሳ አጋጣሚውን ቢያገኙ ብዙ ማለት እንደሚችሉ አስባለው።

እርግጥ ነው ሁላችንም የማንክደው፥ በጉርምስና ወቅት የምናሳየው ያልተገባ ባህሪ ይኖረናል። ወላጆቻንን የማናከብርባቸው ብዙ መንገዶች ቢኖሩም ልብ ብለን በማናስተውላቸው ነገሮች ላናከብራቸው ወይም ልናሳዝናቸው እንችላለን። በምንናገርበት መንገድ፣ በንግግራችን ላይ በምንጠቀምባዘው ቃላት፣ በምናሳየው ያልተገባ ድርጊት እና አኳኋን አለመታዘዛችንን ልናሳይ እንችላለን።

ይህ ትዕዛዝ በእግዚአብሔር ፊት የከበረ በመሆኑ በአስርቱ ትዕዛዛት ላይ ላይ ስድስተኛው ቦታ ይዞ እናየዋለን። ከትዕዛዛትም ውስጥም ደግሞ ከታዘዝነው ረጅም እድሜን እንደሚሰጠን ቃል የገባልን ብቸኛ ትእዛዝ ነው። ይሄ ትዕዛዝ ደግሞ የብሉይ ኪዳን ትዕዛዝ ብዛ አይደለም! በኤፌሶን ምዕራፍ 6 ከቁጥር 2 እስከ 3 ላይ ጳውሎስ “መልካም እንዲሆንልህ ዕድሜህም በምድር ላይ እንዲረዝም አባትህንና እናትህን አክብር፤ እርስዋም የተስፋ ቃል ያላት ፊተኛይቱ ትእዛዝ ናት።” በማለት ዘዳግም 5፥16’ን በቀጥታ ጠቅሶ ተናግሯል።

 

፮ – ስግብግብነት

መጽሐፍ ቅዱስ ሆዳምነትን እንደ ኃጢአት ቆጥሮ ተናግሯል። ነገር ግን ብዙ ክርስቲያኖች በዚህ ጉዳይ ላይ ሆዳምነትን ወይም ስግብግብነትን ከኃጢአት ጎራ ለመመደብ ይከብዳቸዋል። ምናልባት እነሱ በሆዳምነት ወይም በገብጋባነት ከሚፈርጁት ሰው የሚመጣውን ምላሽ በመፍራት ይሆናል። ታዲያ አንዳንዶች እንደሚያስቡት ሆዳምነትን ወይም ስግብግብነት ስናነሳ ሁልጊዜ የምግብ ጉዳይ ሊመጣብን አይገባም።

ስግብግብነትን በምግብ፣ በልብስ፣ በገንዘብ፣ በእውቀት፣ በጊዜ እና በመሳሰሉት ልንገልፅ እንችላለን። እንዲሁም እራስን ብቻ ለማስደሰት “በጊዜ ስግብግብነር” ለጸሎት እና ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መዋል የሚችልን ብዙ ሰዓታትን በማጥፋት፤ የጊዜ ገብጋባነታችንን ልናነሳ እንችላለን።

በአጭሩ ገብጋባነት ማለት እኛ ከሚያስፈልገን በላይ በመፈለግ ሁልጊዜ የማይሞላውን የራሳችንን ፍላጎት ለመሙላት ማግበስበስ ማለት ነው። ይህ ገብጋባነት ደግሞ አድጎ አድጎ ሳናውቀው ወደ ጣዖት አምልኮ ይመራናል! (ያው ሆዳምነትና ጣዖት አምልኮ ወንድማማቾች ባይሆኑም የቅርብ ዘመዳሞች ናቸው።)

 

፯ – ቅዱሳንን ማግለል እና ማራቅ

ይህ ችግር አሁን ላይ በቤተክርስቲያን ውስጥ ትልቅ ችግር እየሆነ መጥቷል። እርግጥ የሰውን ችግር ሆነ በሽታ ከቁብ ሳይቆጥሩ በእውነተኛ ወዳጅነት በፍቅር የሚመላለሱ ሰዎች አሉ። እንደዛውም ደግሞ ትኩር ብለን ከተመለከትን፤ የተጨቆኑ፣ የተራቆቱ፣ የተራቡ፣ የታመሙ እና የተቸገሩ ሰዎችን ማየት የሚያንገሸግሻቸው ሰዎች መኖራቸውን እናስተውላለን! እኛስ የታመመን ለመጠየቅ ምን ያህል ቅርብ ነን? የተቸገረውንስ ለመርዳት? በጣም የሚያሳዝነው እና የሚያናደው ደግሞ በቤተክርስቲያኑ ውስጥ የሚበላውን እና የሚለብሰውን ያጣ አብሮት የሚያመልክ ወገን እያለ፤ አይኑን እና ጆሮውን ደፍኖ እየሄደ ገንዘቡን ለማንም ግንብ እና ቆርቆሮ የሚዘራው ሰው!

ይህ ቸልተኝነት ወይም ሰዎችን ማግለል ከፍተኛ ኃጢአት ነው ምክንያቱም የታመሙትን መጎብኘት የራሱ የክርስቶስ ትዕዛዝ ስለሆነ (የማቴዎስ ወንጌል 25፥36)፤ ነገር ግን በጣም ጥቂት ክርስቲያኖች ናቸው ለሌሎች ማድረግ፥ ለራሱ ለክርስቶስ ማድረግ እንደሆነ የሚያውቁት (የማቴዎስ ወንጌል 25፥40)

 

* * * መደምደሚያ * * *

የዘረዘርኳቸው ነጥቦች ላይ አስርቱን ትዕዛዛት የተጠቀምኩበት ምክንያት እያንዳንዱ የምንፈፅመው ኃጢአት በነዚህ ውስጥ የተገኘ ስለሆነ ነው። የእግዚአብሔርን ሰም በከንቱ ስላለመጥራት፣ እሱን ስለማክበር እና ሌሎችንም መጥቀስ ይቻል ነበር ግን ክርስቲያኖች እነዚህን ነገሮች እንዲፈፅሙ ወይም ደግሞ እንዳይፈፅሙ በግልጽ ስለተነገረ ሳልጠቅስ አልፌያቸዋለው።

ስለዚህም ማናችንም ብንሆን እርስ በእርሳችን መዋሸትም ሆነ በሐሰት መመስከር፣ ሌሎች ማማት፣ የሌሎች የሆነን ነገር መመኘት እና መስገብገብ የለብንም! ባለን ነገር መርካት አለብን (ፊልጵስዩስ 4፥11-13)! ወላጆቻችንን ማክበር እና መታዘዝም ደግሞ ጥያቄ ውስጥ በማይገባ መልኩ ልንተገብረው ይገባናል!

ሃሳቤን በጥያቄ ልቋጭ። እናንተስ በክርስቲያኑ ማህበረሰብ ውስጥ ያስተዋላቹሃቸው ችላ የተባሉ እና የተለመዱ ኃጢአቶች የምትሏቸው ምንድናቸው? ስለነሱስ ምን ታስባላቹ? ከትህትና ጋር!

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

x

Check Also

የእውቀት እና የእውነት መልክ

በአሹቲ ገዛኸኝ   ክቡድ በሆነው ምሽት ላይ “ሰውየውን በሕይወት እና በሞት መካከል ደብድበውት ጠፉ” ይለናል፣ ...

%d bloggers like this: