Home » Articles » ተቀብቼአለሁ!

ተቀብቼአለሁ!

በአሳየኸኝ ለገሰ

በእድሜዬም ሆነ በመንፈሳዊ ሕይወቴ ‹‹ልጅ›› በነበርኩበት ወቅት፤ አንዳንድ ሚስጥር የሚገለጥላቸው (መገለጥ ያላቸው) አገልጋዮች ይህን ሲሉ ከምንም ነገር በላይ እደሰት ነበር፤–

“ዛሬ በዚህ ጉባኤ መካከል በልዩ ቅባት የምትቀቡ ሰዎች አላችሁ!!” –ሲሉ— አቤት! ‹ያ ሠው እኔ እሆን ይሆን!?› እላለሁ፡፡
በልዩ ቅባት መቀባት ማለት እንደነርሱ ምስባኩን ተቆጣጥሮ መድመቅ እንደሆነ አስብናም፤ ቀን ከሌት ይህ “ልዩ ቅባት” እንዲሰጠኝ ወደ አምላኬ እፀልያለሁ፡፡…. ‹‹ተራ ምዕመን መሆን አልፈልግም›› እለዋለሁ፡፡ ዝም ብሎ ቃል ሰብኮ የሚወርድ አገልጋይም መሆን እንደማልፈለግ እነግረዋለሁ፡፡ በሄድኩበት ስፍራ ሁሉ ልዩው ቅባት መጥቶ ነውጥ እንዲፈጥር እፈልጋለሁ፡፡

ለምሳሌ፤ ታክሲ ውስጥ ስገባ ጥቁር ሂጃብ የለበሰች ሴት ‹‹ኡ! ኡ! አቃጠለኝ!›› ብላ ስትጮህ በምናቤ አስላለሁ፡፡ ትምህርት ቤት ‹‹እግዚአብሔር የለም!›› እያለ አፉን የሚከፍተው ባዮሎጂ አስተማሪያችን (በፊቴ መቆም ተስኖት) የተጠናወተው የክህደት መንፈስ (በተማሪው ሁሉ ፊት) እየጮኸ አንፈራግጦ እንዲለቀው እመኛለሁ፡፡… እኔ ባለፍኩበት መንገድ ሁሉ አይነ-ስውሩ እንዲያይ፣ ሽባው እንዲተረተር፣ ጨርቁን የጣለው እብድ ልቡ ተመልሶለት ጨርቁን ፍለጋ ቤቱ እንዲመለስ እመኛለሁ……  !!…….. ይህ ብቻ አይደለም፡- ጨቋኝ የአገር መሪዎችን፣ አራጣ አበዳሪዎች፣ ስግብግብ ነጋዴዎችን፣ ጠንቋዮችን፣ ወደ ቸርቻችን ጣራ ድንጋይ የሚወረውሩትን  …..(ወዘተ) ቃል እያወጣሁ መረፍረፍ ያምረኛል፡፡ (በልዩው ቅባት ነው እንግዲህ ይህን ሁሉ የማደርገው!)  ልብ-ወለድ እያስነበብኳችሁ እንዳይመስላችሁ፡፡ እንዲሆንልኝ ተግቼ የጸለይኩበትን ነገር ነው ምነግራችሁ፡፡….. ሰባኪያኑ፤ ‹‹ልዩው ቅባት ሲመጣ ልዩነትን ይፈጥራል!›› ሲሉ የነገሩኝ፤ ቅባቱ እነዚህን ሁሉ ታላላቅ ተአምራቶች እንደሚያደርግ ነው፡፡

እጸልይ ነበር…. እጾም ነበር…. ለመቀደስ እጥር ነበር….—– ለመቀባት ከኔ የሚጠበቀውን ሁሉ አደርግ ነበር!!
ከዕለታት ባንዱ ግን–እምነቴን የሚያናጋ የሚመስል አንድ ነገር ሰምቼ ደነገጥኩ፤ ግለቴ ላይ ውሃ የቸለሱብኝ መሰለኝ፡፡ አንድ አባት ናቸው፡፡ ሊጠይቁን ቤታችን በመጡበት፡-  “ወደፊት ምን መሆን ትፈልጋለህ?” ብለው ጠየቁኝ፡፡ “በልዩ ቅባት መቀባት!” ብዬ መለስኩላቸው፡፡

‹‹በጣም ጥሩ ነው ልጄ!” ብለው ፈገጉልኝና ዝም አሉ፡፡ ….. ተሰናብተውን ከቤት ሲወጡ ግን፣ ‹‹ጎረምሳው! ና ሸኘኝ!›› ብለውኝ ልሸኛቸው ወጣሁ፡፡
“ልጄ!… የጌታን ቅባት መውደድህን አድንቄአለሁ!” አሉኝ ከግቢያችን ወጣ እንዳልን፡፡ “ግን እኮ አሁንም ተቀብተሃል!” አሉኝ ደግሞ አስከትለው፡፡
“አሁንማ አልተቀባሁም፡፡ ወደፊት ጌታ እንደሚቀባኝ ነው መልዕክት የመጣልኝ!” አልኳቸው መልሼ፡፡
“መልካም!፤ ቃሉ የሚለውን ግን ልንገርህ…. በክርስቶስ ያመንን ሁላችንም ከ‹ቅዱሱ ቅባት› ተቀብለናል!!፡፡ ይህም ቅባት ሁላችንም የጠጣነው አንዱ መንፈስ ቅዱስ ነው!” ፡፡ …(እኚህ ሰውዬ ግራ ሊያጋቡኝ ነው እንዴ ሸኘኝ ብለው ከቤት ያስወጡኝ??)

“መንፈሱንማ ተቀብያለሁ፡፡ ግን ገና ልዩ ቅባትም እቀበላለሁ!” አልኩኝ፤ እርግጠኝነት በሚነበብበት ድምጸት፡፡………
“ልጄ! የተቀበልነው አንዱ ቅባት እርሱም መንፈስ ቅዱስ፣ እንደወደደ የሚያከፋፍለው ልዩ ልዩ ጸጋ እንጂ ‹‹ልዩ›› የሚባል ቅባት በአዲስ ኪዳን የለም፡፡…..ለምሳሌ፤– ነብይነት ልዩ ቅባት አይደለም፤ የቅዱሱ ቅባት አንዱ አገልግሎት እንጂ፣…ሠባኪነትም ልዩ ቅባት ሊሆን አይችልም፤ሁላችንም የጠጣነው አንዱ መንፈስ ለአንዳንዶች የሚሰጠው የጸጋ ስጦታ እንጂ፣…. ተአምራት ማድረግም ልዩ ቅባት አይደለም፤ ከዛው ቅባት ላይ ተጨልፎ ለአካሉ መታነጽ ለአንዳንዶች የተሰጠ ስጦታ እንጂ……..”…..
እርፍ!!  ………………..
ነገር አለሙን አዟዟሩብኝ፡፡ …… እያደር ግን እያቃረኝም ቢሆን እውነቱን ጠጣሁት፡፡ ……ጸሎቴን ቀየርኩ…..፡፡ እነዚያ ሰዎች ግን አሁንም ተመሳሳይ መልዕክት ማምጣታቸውን አላቆሙም፡፡ …

“ዕጣህ እዚህ አይደለም ከፍ ከፍ ትላለህ!”…… “ከአሁን በኋላ እዚህ አትገኝም!…” …”ባንተና በሌላው መካከል ልዩነት መጥቷል!”….”እንደ ንስር በከፍታ ትበራለህ!…” (ወዘተ) ይሉኛል፡፡ …..(ርግጥ ስለ እኔ ዕጣ-ፈንታ ዕጣዬን የወሰነው መንፈስ ቅዱስ የገለጠላቸውን የነገሩኝ ሊኖሩ ቢችሉም፤ ይህ በአማኞች መካከል ‹‹ምድብ›› (class) የመፍጠር ልማድ ግን አዲስ ኪዳናዊ መሰረት የሌለው መሆኑን ስለተረዳሁ፣ እንደድሮው ‹‹ያዙኝ ልቀቁኝ››ን ተውኩ፡፡)
እስካሁን ወዴትም አልበረርኩም፡፡ እውነቱ ይሄው ነው፡፡  ያገለግል ዘንድ የተጠራ ሁሉ መንጋውን ለማገልገል ይበልጥ ወደ መንጋው ይቀርባል እንጂ ወዴትም አይበርም!፡፡ ….. ‹‹ልዩነት ሆኖልሃል!›› የተባለለትም ሰው፤ ድኩም የጌታ ሎሌና የሕዝቡ አገልጋይ እንጂ ልዩ ሰው ሊሆን አይችልም!!….. “ከፍታ ይሆንልሃል!” የተባለለትም ቢሆን፣ ሁላችንም በክርስቶስ በሰማያዊ ስፍራ በጸጋው ከተሰጠን የሚበልጥ (ከፍ ያለ) መቀመጫ ሊገኝለት አይችልም!!፡፡…   የትኛውም የጸጋ ስጦታ ምድብ (class) ፈጥሮ ራስን መስቀያ ሳይሆን፣  በሎሌነት መንፈስ ክርስቶስ የሞተለትን ሕዝብ ማገልገያ ነው!፡፡
እናም….. ወንድሜ ደስ ይበልህ፤ እንዳልተቀባህ ወይም ገና እንደምተቀባ የሚነግሩህን ተዋቸው፤ ቃሉ ተቀብተሃል! ይልሃል፡፡…ኢየሱስን ያመንሽና በመንፈሱ የታተምሽ አንቺም እህቴ የተቀባሽ ነሽ! ደስ ይበልሽ!…..
እኔስ??…. ቀላል ተቀብቼአለሁ እንዴ!!??….
ለቀባን ለእርሱ፣ ለእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ፤ ክብር፣ ኃይል፣ እዘዝና አምልኮ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይሁን!!—አሜን!!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

x

Check Also

የእውቀት እና የእውነት መልክ

በአሹቲ ገዛኸኝ   ክቡድ በሆነው ምሽት ላይ “ሰውየውን በሕይወት እና በሞት መካከል ደብድበውት ጠፉ” ይለናል፣ ...

%d bloggers like this: