Home » Articles » አማራጭ ድልድዮች!

አማራጭ ድልድዮች!

አማራጭ ድልድዮች!
በአሳየኸኝ ለገሰ

ሪቻርድ ፎስተር “the religion of the mediator” ሲል ይጠራዋል፤ አንዳንድ “አገልጋዮች” በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ልዩ “የስልጣን እርከን” እንደተሰጣቸው የሚታሰብበትን ስርአት፡፡ እነዚህ ሰዎች ልዩ ልዩ መገለጫዎች አሏቸው፡፡
ሲጀምሩ፣ እግዚአብሔር በተለየ መንገድ ራሱንና ቃሉን እንደገለጠላቸው አድርገው ራሳቸውን በማቅረብ ይጀምራሉ፡፡

ቃሉን ከነአካቴው ዘግተው በግላቸው “መንፈስ ቅዱስ ገለጠልን” ያሉትን ትኩስ መገለጥ ያቀርባሉ፡፡ ቃሉን ከፍተው ያነበቡ እንደሆነም የሚያነቡትን ክፍል ያው መንፈስ ብዙዎች በማያዩት “ልዩ መንገድ” (የክፍሉ አውድ ከሚናገረው ውጪም ቢሆን) እንዳስተማራቸው በድፍረት ይናገራሉ፡፡

አማኙ ክርስቲያንም ዘወትር በእነርሱ በኩል የሚተላለፍለትን “ትኩስ መልእክት” እና “አዲስ መገለጥ” በንቃት ከመጠበቅ በዘለለ በግሉ ቃሉን እንዲያጠና አይበረታታም፡፡ የመንፈስን አብርሆት ሊያገኝ እንደሚችልም አይቆጠርም፡፡

ቻርለስ ስፐርጀን አዳዲስና ትኩስ መገለጦችን ስለሚያመጡ ሰዎች ሲናገር፣ “የውሸት ነገረ-መለኮት ካልሆነ በስተቀር፣ ከተገለጠው ውጪ አዲስ ነገረ-መለኮት ሊኖር አይችልም!” (“there is no new theology unless it is false.”) ሲል እነዚህ ሰዎች ለቃሉ ስልጣን መገዛት እንደሚገባቸው ይናገራል፡፡

አማኞች የነርሱ ጥገኛ እንዲሆኑ የሚያደርጉባቸው ሌሎችም መንገዶች አሏቸው፡፡ ለምሳሌ፡- ሰዎች እንዲጸልዩ ከማበረታታት ይልቅ “እኔ ጸልይልሃለሁ፤ አንተ የራስህ ጉዳይ ላይ አተኩር” ሲሉ…. ሰውን ወደ ክርስቶስ ከመምራት ይልቅም “ልተንብይብህ” … “እጅ ልጫንብህ”… “ቃል ላውጣብህ” በሚሉ ማባበያዎች ሲደልሉት ሊገኙ ይችላሉ፡፡ ራሳቸውን  ከእግዚአብሔር ዘንድ ለመፍትሔ እንደተላኩ አድርገው ስለሚያቀርቡም ሕዝበ-ክርስቲያኑ በነርሱ በኩል የሚመጣለትን በረከት ከመጠበቅ ውጪ በግሉ ወደ አምላኩ የማይገሰግስ አቅመ-ቢስ እንዲሆን ያደርጉታል፡፡

ምስባኩን ሲይዙት፤ ብዙ ጊዜያቸውን የሚያውሉት ለየት ያሉ መንፈሳዊ ልምምዶቻቸውን አብዝተው በመናገርና ለእግዚአብሔር ያላቸውን የተለየ ቅርበት በማስረዳት ነው፡፡

እኛ ከእግዚአብሔር ዘንድ የምንፈልውን ሁሉ እንደሚያቀርቡልን ይነግሩናል፡፡ “ከመለኮት አገናኝ ኦፕሬቶሮቻችን” ስለሆኑም፣ ማንንም ወደ ክርስቶስ ሳይሆን ወደራሳቸው ይጠራሉ፡፡ እነርሱ “የበቁ ጻድቃን” ናቸው፤ ስለሆኑም “የመንፈስ ቅዱስ የሃይል ማዕከል” ተደርገዋል፡፡ ጨርቃቸውን እየነካንና በ‹‹እፍፍ…›››ታቸው እየተጠቀምን ኃይልን እንድንሞላ ይጋብዙናል፡፡ ከአምላክ ዘንድ የተቀበሉትን ዘይት በቀንዳቸው ሞልተው እንደሚጠብቁን ከፍ ባለ ድምጽ ያበስሩናል፡፡  እኛም ይህን አምነን በቅርባችን ካሉልን በደብራቸው እንድንጠለል በቅርባችን ከሌሉም አሉ የተባሉበትን ሁሉ በማሰስ እንዲፈልጋቸው አዳራሾቻቸውን ክፍት አድርገው ይጠሩናል፡፡

ርግጥ የአገልጋዮችን ጸጋ ለመካፈል የትም መሄድ አይኖርብንም ሊባል አይገባም፡፡ ሰውን ሁሉ ለድኀነትና ለሕይወት “ማንም…ወደ እኔ ይምጣ!” ወዳለው ጌታ ከመጠቆም ይልቅ ወደ ራሳቸው ወደሚጠቁሙት ግን ላለመሄድ ቁርጥ ውሳኔ ያስፈልጋል፡፡

ልጆች የሆንን ሁላችን በመንፈሱ እግዚአብሔርን “አባ አባት” ብለን እንድንጠራውና ከእርሱ ጋር ቅዱስ ተራክቦ እንድናደርግ የተሰጠንን የልጅነት መብት እንዳናስተውል በመርዛማ ትምህርቶቻቸው ከሚሸፍኑብን፣ የሁሉ የበላይ የሆነ ሊቀ ካህናት እርሱም ክርስቶስ ብቻ እንደሆነ፤ የሱ የሆንን ሁላችንም ከርሱ  ክህነትን እንደተቀበልን ከማይነግሩን፣ ምህረትን እንድንቀበል፣ በሚያፈልገንም ጊዜ ሁሉ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ በቀጥታ ወደ ሊቀ ካህናቱ የመሄድና በእምነት እርሱን የማናገር መብት መጎናጸፋችንን እንዳናስተውል አዚም ከሚረጩብን፣ ከእነርሱ ራሳችንንም ሆነ ሌሎችን ልናድን ይገባል!

እግዚአብሔር ከአንድ ልጁ በስተቀር እኛን ወደ እርሱ ለማቅረብ የገነባቸው አማራጭ ድልድዮች የሉትም፡፡ ራሳቸውን በዚህ መልክ በማቅረብ ዋናውን ድልድይ እንዳናይና በእርሱ ስራ እንዳንደገፍ ልቡናችንን የሚሰልቡትን ቢቻል መሞገት፣ ካልተቻለም ከቀለሱት የአምልኮተ-ሰብ ቤታቸው አውጪኝ እግሬ ብሎ መሸሽ ያስፈልጋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

x

Check Also

የእውቀት እና የእውነት መልክ

በአሹቲ ገዛኸኝ   ክቡድ በሆነው ምሽት ላይ “ሰውየውን በሕይወት እና በሞት መካከል ደብድበውት ጠፉ” ይለናል፣ ...

%d bloggers like this: