Home » Articles » እግዚአብሔር ሰጠ፤ ሰይጣን ነሳ!

እግዚአብሔር ሰጠ፤ ሰይጣን ነሳ!

(አሳየኸኝ ለገሰ)

በርካታ የእምነት እንቅስቃሴ አራማጆች ኢዮብ መከራን በራሱ ላይ ያመጣው በገዛ አንደበቱ አሉታዊ ንግግር በመናገሩ ነው ይላሉ፡፡ ቻርለስ ካፕስ የተባለ የእምነት እንቅስቃሴ አራማጅ፡- “ኢዮብ በአንደበቱ ቃል እና በልቡ ፍርሃት ሰይጣን እንዲያጠቃው በር ከፍቷል፡፡ የእምነት ቃል እግዚአብሐርን ወደ ሁኔታችን ያመጣዋል፡፡ ፍርሃት ግን ሰይጣንን ይጋብዛል፡፡ ኢዮብ ፈርቶ ነበርና የፈራው ደረሰበት!” ይላል፡፡ ለዚህም አሳቡ በኢዩብ 3፡25 ‹የፈራሁት ነገር መጥቶብኛልና፤ የደነገጥሁበትም ደርሶብኛል› የሚለውን የኢዮብን ቃል ይጠቅሳል፡፡ አክሎም፤ “ኢዮብ እግዚአብሔር ሰጠ፤ እግዚአብሔር ነሳ ብሎ የተናገረው በመንፈስ ሆኖ አይደለም” ይላል፡፡

 

ኬኔት ኮፕላንድም “ኢዮብ መከራ እንዲቀበል እግዚአብሔር ፈቅዷል ስለምን እንላለን?ሰይጣን እንዲያጠቃው ያደረገው እራሱ ኢዮብ ነው፡፡” ሲል ይናገረል፡፡  አገር በቀሉ ዘላለም ጌታቸው የተባለ የነዚህ ቀንደኛ መናፍቃን “ካርቦን ኮፒ” የሆነ ሰውዬም (ራሱን “ሐዋሪያ” ብሎ የጠራበትን ማዕረግ አልጠቀምም!) ጻድቁን ኢዮብን ሲያብጠለጥል እያዘንን መስማታችን ይታወሳል፣ ኢዮብን ለመስደብ አፉን በከፈተ ጊዜ ከአፉ የወጣችው ስድብ ራሱን የምትገልጽ መስላ አረፈችው እንጂ።

 

የእነዚህን ሰዎች ንግግር ስናጤን፣ የኢዮብ ታሪክ “በበሽታም ሆነ በሌሎች ልዩ ልዩ ፈተናዎች እንድንፈተን እግዚአብሔር አይፈቅድም!” የሚለውን ስኁት ድምዳሜያቸውን አፈር ከድሜ ስለሚያስግጥባቸው ትምህርታቸውን ለመከላከል የፈጠሩት ቅዠት መሆኑን መረዳት አያቅትም፡፡ እግዚአብሔር ራሱ፤ “ፍጹም፣ ቅን፣ እግዚአብሔርን የሚፈራ፣ ከክፋት የራቀ” ሲል የመሰከረለትን ሰው ስለ አለማመንና ስለ ፍርሃት መክሰሳቸው እና ‹‹ኢዮብ እግዚአብሔርን በአንድ ጊዜ ሰጪም ነሺም አድርጎ በማቅረቡ ‘የሳተ ነቢይ’ ነው” ማለታቸው ከዚህ የመነጨ ነው፡፡

 

እውነቱ ግን በመከራ ውስጥ ለሚያልፉ ሰዎች ከምንም በላይ የኢዮብ ታሪክ ከፍተኛ ፋይዳ ያለው መሆኑ  ነው፡፡ አንዳንዶች እንደሚያስቡት የኢዮብ መጽሐፍ ጥቃትንና በሽታን ተቀብሎ መኖርን የሚያበረታታ አይደለም፡፡ ይልቁንም በትዕግስት መጽናትንና እምነትን የሚያስተምር ነው፡፡ የኢዮብን ታሪክ ስናነብ ጽናትን እናያለን፡፡ የኢዮብን ታሪክ አንብቦ ኢዮብን ያጸናውን ጸጋ ላያደንቅ የሚችል ማነው?፡፡ ዶግላስ ኮነሊ የተባሉ መምህር ሲናገሩ፤ “ሰይጣን ኢዮብን (በፈተናው) ለመጣል የሚያስፈልገውን ሁሉ ሲያዘጋጅ፣ እግዚአብሔር ደግሞ ኢዮብ ፈተናውን ድል እንዲነሳ የሚያስፈልገውን ሁሉ አዘጋጀ!” ብለዋል፡፡ ያለ እርሱ ጸጋ ምን ያህል ደካሞች እንደሆንን እንድናስተውልና በእርሱ ጸጋ ብቻ ግን ሁሉን እንደምንቋቋም ለማስተማር እግዚአብሔር መከራን ይጠቀምበታል፡፡

 

የኢዮብ ታሪክ በፈተና ወቅት በእግዚአብሔር ብቻ ተስፋ ማድረግንና በእርሱ መደገፍን ያስተምራል፡፡ በራስ ጥበብም ሆነ በሰው እርዳታ የሚመጣ መፍትሔ በጠፋበት ሰዓት በእግዚአብሔር ብቻ መታመንን ከዚህ መጽሐፍ እንማራለን፡፡ በተለይም በሕመም አልጋቸው ላይ ለሚማቅቁ የኢዮብ ታሪክ ጮኾ የሚናገረው ይሄንኑ እውነት ነው፡፡ አንድ ሰው ሲናገር፡- “በህመም አልጋችን ላይ በጀርባችን ተንጋለን ስንተኛ፣ የምናየው አንድ ቦታ ወደ ላይ ብቻ ነው!” ብሏል፡፡ ለዚህም ኢዮብ ምስክር ነው፡፡ “ስጋዬን በጥርሴ እይዛለሁ ቢገድለኝም እርሱን እጠብቃለሁ” ሲል ወደ ላይ ማየቱን ወይም በእግዚአብሔር ብቻ ተስፋ ማድረጉን እናስተውላለን!!

 

በመከራ ሲያልፍ በእግዚአብሔር ተስፋ ማድረግን የተማረ ሰው ደግሞ ከመከራ በወጣም ቀን የሚመካው በእግዚአብሔር ጸጋ ብቻ ነው፡፡ “ከመከራ የተማረ ሰው ጉልበቴ፣ ብርታቴ፣ ጾም ጸሎቴ፣ የቃል እውቀቴ፣ ትጋቴ፣ እኔ… የማለት ዝንበሌ አይኖረውም፡፡”
ሲ ኤስ ሉዊስ “እግዚአብሔር በምቾቶቻችን ሰዓት ለህሊናችን በሹክሹክታ ይናገረናል፡፡ በመከራ ጊዜ ግን ከፍ ብሎ በሚሰማ ድምጽ ይናገረናል፡፡ መከራ እግዚአብሔርን ከመስማት ለሚዘገየው ዓለም የእግዚአብሔር ድምጽ ማጉያ መሳሪያ ነው!!” ብሏል፡፡

 

አንዳንዶች “ኢዮብ በአዲሱ ኪዳን ከምንኖረው ከእኛ ይለያል፤ እኛ በክርስቶስ የመገረፍ ቁስል የተፈወስን ሰዎች ስለሆንን በሽታን በእምነት መቃወም ይኖርብናል!” ይላሉ፡፡ በክርስቶስ ቁስል ስለመፈወሳችን የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍልም ስለ ስጋዊ ፈውስ የተነገረ እንደሆነ በመናገር ይከራከራሉ፡፡
ሐዋሪያው ጴጥሮስ ይህን ክፍል በ1ጴጥ 2፡14-15 ላይ በማንሳት ስለ ፈውሱ አይነት በሚገባ አብራርቷል፡፡ “ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር፥ እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ፤ በመገረፉ ቁስል ተፈወሳችሁ። እንደ በጎች ትቅበዘበዙ ነበርና፥ አሁን ግን ወደ ነፍሳችሁ እረኛና ጠባቂ ተመልሳችኋል።” ሲል። ይህ ክፍል በማያወላዳ መልኩ ክርስቶስ ኃጢአታችንን የተሸከመው ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ የምንኖርበትን አዲስ ልደት እንድናገኝ እንደሆነ ይናገራል፡፡ በመገረፉ ቁስል መፈወሳችን ያስገኘልን ጥቅምም ወደ ነፍሳችን እረኛ የመመለስና ከእርሱ የመታረቅ እንደሆነ ተናሯል፡፡ ጴጥሮስ የክርስቶን መገረፍና ሞት ከስጋዊ ፈውስ ጋር በቀጥታ ሲያገናኘው አናይም፡፡ የክርስቶስ መገረፍና ሞት አላማው የሰው ልጆችን ኃጢአት ማስወገድ ነውና፡፡

 

ክርስቶስ ኃጢአታችንን ባስወገደበት መንገድ ህመሞቻችንን እንዳስወገደ የሚያስረዳ አንድም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የለም፡፡ የክርሰቶስ መሞት አላማ ስጋዊ ፈውስን ማረጋገጥ ቢሆን መሞት አያስፈልገውም፡፡ ስጋዊ ፈውስን ሳይሞትም በፊት መስጠት ችሏልና! የኃጢአትን ስርየትን ሊሰጠን የሚችለው ግን ደሙን በማፍሰስ ብቻ ስለሆነ ሞተልን፡፡ “ደምም ሳይፈስ ስርየት የለም!”፡፡ አንድ ሰው ሲናገር፡- “የእግዚአብሔር ዋነኛ ጥል ከእኛ ሕመምና ድህነት ጋር ቢሆን ኖሮ ጳውሎስ ‹‹እግዚአብሔር ሕመምና ድህነት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ሕመምና ድህነት አደረገው!›› ብሎ ይጽፍልን ነበር!” ብሏል፡፡

 

ይህ ማለት ግን እግዚአብሔር ስለ ስጋዊ ሕመማችንና መከራችን ግድ የማይሰጠው ነው ማለት አይደለም፣ በጭራሽ!፡፡ እግዚአብሔር ለአካላዊ ጤንነታችን ግድ የሚለው አባት ነው፡፡ ከራሳችን ጸጉር አንዲቱ እንኳን ያለ እርሱ ፈቃድ መሬት ላይ አትወድቅም፡፡ እግዚአብሔር በታመምን ጊዜ ፈዋሻችን ነው፡፡ ምናልባት ለተለየ አላማው በልዩ ልዩ መከራ እንድንፈተን ቢፈቅድ አንኳን የማይራራ ጨካኝ አምላክ ስለሆነ አይደለም፡፡ መልሶ የሚምርና ከፈተናው ጋር መውጫን ደግሞ የሚያዘጋጅ ነውና፡፡

 

በመጨረሻም፤- ‘እግዚአብሔር መከራን ወይም ፈተናን ሊፈቅድ ይችላል’ ብዬ ብቻ ጽሑፌን ብዘጋ ምሉዕ ትምህርት አላስተላለፍኩም፡፡ “እርሱ ፈተናውን ይቆጣጠራል!” ልል ደግሞ ይገባኛል፡፡ እንደ አማኞች ይህ ተስፋ አለን፤ ሁሉም ነገር በአምላካችን በእግዚአብሔር ቁጥጥር ስር ነው፡፡ ዋረን ዌርዝቢ እንዳሉት፤ “እግዚአብሔር፣ ሰይጣን ምድጃውን እንዲለኩስ ሲፈቅድለት ሙቀት መቆጣጠሪያውን ሁል ጊዜ በእጁ ይዞ ነው!”፡፡ እርሱ በውሆች ውስጥ ባሳለፈን ጊዜ ከልክ በላይ እንዳይፈሱ ይቆጣጠራል፡፡ ልጆቹንም በድል ያሻግራል፡፡ ኢዮብ በአንድ በኩል ቢገድለው እንኳን እግዚአብሔርን እንደሚጠብቅ እየተናገ በሌላ በኩል ደግሞ እግዚአብሔር ሳይገድለው በወሰነው ሰዓት መከራውን ድል እንደሚያስነሳው የነበረውን ተስፋ ይናገር ነበር፡፡ “ከፈተነኝም በኋላ እንደ ወርቅ እወጣለሁ” (23፡10) ሲል የመከራው ትሩፋት እንደ ወርቅ በእሳት የተፈተነ እግዚአብሔርን የሚመስል ሕይወት እንደሆነ ተናግሯል፡፡ ለእኛም የሚሆነው እንዲሁ ነው፡፡ እግዚአብሔር ተፈትኖ የወጣ እምነታችንን ይፈልጋል፡፡

 

ፊሊፕ ያንሲ፤  ‹‹ደህና አድርጎ የተንከባከበኝን እግዚአብሔርን እከተላለሁ›› ከሚለው ‘የኮንትራት እምነት’ ፣ የትኛውንም መከራ ሊቋቋም ወደሚችል የእምነት ደረጃ መሸጋገር የሚኖርብን ወቅት እንዳለ ይናገራሉ፡፡ መስቀላችን በጊዜው ወደኛ በመጣ ጊዜ መሸሽ የማይኖርብን ለዚህ ነው፡፡

 

ክርስትና ሀዘንተኞች በምንሆንባቸው ወቅቶች እንኳን ከጌታ የተነሳ ዘወትር ደስ የምንሰኝበት ሕይወት ጭምር እንጂ ሃዘን አልባ፣ ከዓለም የተነጠለ ሰላማዊ ደሴት ላይ የምንኖረው ሕይወት አይደለም፡፡ በፈተናችን ሰዓት የክርሰቶስ ኃይል ያድርብን ዘንድ በድካማችን እንድንመካና ሃሴት እንድናድርግ ታዘዘናል (2ቆሮ 12፡9)። ድካምንና ፈተናን ሁሉ ጤናማ ባልሆነ እምነት መቃወም ይህን እውነት መዘንጋት ነው፡፡

 

“የብልጽግና ሰባኪያን የሚታወቁት የኢዮብን 40 ምዕራፎች ገሸሽ አድርገው 42ኛውን በመስበክ ነው፡፡” በተአምራዊ ፈውስ ከበሽታ ማምለጥን የመጨረሻው ግብ አድርገው ያስተምራሉ፡፡ ይሁን እንጂ ፍጹም የሆነው ከበሽታ ነጻ መውጣት የሚገኘው በተአምራዊ ፈውስ ሳይሆን ክርስቶስ ሲመጣ በሚሆነው ተአምራዊ የስጋ ትንሳኤ ነው፡፡ ሕመምና መከራ እስከወዲያኛው የሚወገደው በሚመጣው ዓለም የሚሞተው የማይሞተውን ሲለብስ፣ የሚበሰብሰውም የማይበሰብሰውን ሲለብስ ብቻ ነው፡፡ ይህ ታላቅ ተስፋ ነው፡፡ ይህን በማስተማር አማኞችን ማጽናናትና ጊዜያዊው መከራ፣ መከራ የሌለባትን አዲስቱን ኢየሩሳሌም እንዲናፍቁ ምክንያት እንዲሆናቸው ማበረታታት ያስፈልጋል፡፡

 

ጳውሎስ ፈቃዱ ይህን ይላል፤

“በእኛም ሆነ በአካባቢያችን የተለያዩ ችግሮችን ባናይና ሁሉ ቢሞላልን የጌታን መምጣት ተስፋ ማድረጋችን ራሱ አጠራጣሪ ነው፡፡ ለማዶች ነን፤ ምድርን እንለምዳለን፤ ከተመቸን እዚሁ መቆየት እንፈልጋለን፡፡ መከራው ግን የድሉን ጌታ መምጣት እንድንናፍቅ ያደርገናል፡፡” እንዲህ ብሎም ያክልበታል “የዘመናችን ቤተክርስቲያን ግን ስለ መከራ ለመናገር፣ ስለ መከራ ለማስተማር፣ ስለ መከራ ሕዝቧን ለማንቃት ፍላጎት ያላት አትመስልም፡፡ የመከራ ርዕሰ ጉዳይ ከተነሳም ጥረቷ መከራን እንዴት መቃወም እንደሚቻል እንጂ መከራው ምን አስተምሮን እንደሚያልፍ ለመናገር አይደለም፡፡ በመከራ ላሉትም ምን ማድረግ እንደሚገባ የሚያስተምር ዝግጅት የለንም፡፡” ይህ እውነት በርቱዕነትና በግልጽነት የጌታ ደቀመዛሙርት ለሆኑት ሁሉ ሊነገርና ሊታመን የተገባው ነው፡፡

 

እንግዲህ ከኢዮብ በመነሳት ይህን ሁሉ ስናገር ስለ እርሱ (ስለ ኢዮብ) ከመናፍቃኑ በተቃራኒ እንዲህ ብዬ ብደመድም መልካም ይመስለኛል፡- ኢዮብ ሰይጣን እንደከሰሰው ሁሉ ዛሬም የሚከሱት ባይጠፉም እርሱ ግን፣ (ጭንቅላታቸውን ለትምህርት ዝግ አድርገው አፋቸውን ክፍቱን የተውት አንዳንድ ግለሰቦች እንደሰደቡት ሳይሆን) በእምነት የመጽናትና የትዕግስት ምሳሌ ሆኖ በሕያው ቃሉ ማህደር የሚኖር፤ አምላኩ እንደመሰከረለትም ፍጹምና ጻድቅ ሰው ነው!!፡፡

 

የግርጌ ማስታወሻ

. Douglas Connely, what the bible says Miracles, (USA, Intervasrsity Press, 1997) 84-85, 85, 133

. Femi Adeleye, Preachers of a Different Gospel, (HippoBooks, 2011) 65
. ጳውሎስ ፈቃዱ፤ የብርሃን አንጓዎች (አዲስ አበባ፣ 2004 ዓ.ም) 22-23፣ 24፣ 25፣ 27
. John Piper and Justin Taylor(General editors), suffering and the sovereignty of God, 121
. Warren W. Wierzbe, The strategy of Satan: How to detect and defeat him, (USA, Tyndal House, publishers, Inc., 1979) 47
. ፊሊፕ ያንሲ (ትርጉም በግርማይ)፣ “ቅይማት” (SIM Publishing) ገጽ 145
. ንጉሴ ቡልቻ፤ መስተአየት፡ ራስ ታዘብና ተሓድሶአውያን መጣጥፎች፣ (አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 2002 ዓ.ም) 96

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

x

Check Also

Fikadu Borena Week Four

Related

%d bloggers like this: