Home » Articles » ዊል ስሚዝ እና ቅዱስ ጳውሎስ

ዊል ስሚዝ እና ቅዱስ ጳውሎስ

ዊል ስሚዝ እና ቅዱስ ጳውሎስ

በአሹቲ ገዛኸኝ

ለፊልም ብዙ ትኩረት የለኝም፣ ካየሁም መርጬ ባይ ነው የምሻው። እናም መርጬ ካየኃቸው ፊልሞች ውስጥ “The pursuit of happines” የሚለውን ዊል ስሚዝ የሚሰራበትን ፊልም በጣም እወድለታለው። አቤት ትወና! እውነት ለመናገር በእሱ የእድሜ ደረጃ እንደዚህ ግሩም አድርጎ የሚተውን አላየሁም፣ አይቻለው እንዴ? አይመስለኝም። ይህ ብቃቱ ያሳመናቸውም ፈረንጆቹ “የጥቁር ፈርጥ” ይሉታል። በእርግጥ እኔም እስማማለው “የጥቁር ፈርጥ ዊል ስሚዝ!”

 

I am Legend

ከላይ የጠቀስኩትን ፊልም ብወደውም አሁን ግን ላወራበት የፈለኩት ፊልሙ ሌላኛውን ነው፤ “I am legend” የሚለውን። እናንተ የፊልም ተዋናይ ሆናችሁ እንበልና በአንድ ከተማ ውስጥ የሚያወራቹ አጋዥ ተዋናይ ሳይኖር ፊልሙን እንደ አንድ ከተማ ተወጡት ብትባሉ ምን ይውጣቹ ይሆን? እናማ ዊል በዚህኛው ፊልሙ አንድ ከተማ የሚሞላ ብቃቱን ይዞ ከች አለ። እንዴት አትሉኝም? ሰውዬው ዊል ነዋ! (ዝም ብዬ ሳዳንቅ።) ስለ ፊልሙ ብዙ ትንታኔ ባልሰጥም፣ አይታችሁታል ብዬ በማመን፣ የፊልሙን ዋና አካል እና ጥቂት ሃሳቦቹን ልናገርበት።

 

ስለፊልሙ በጥቂቱ

ከተማው ላይ በተለቀቀው ገዳይ ቫይረስ ምክንያት ብዙዎቹን ከጨለማ ውጭ በብርሃን የማይወጡ አውሬ አድርጎ ቀየራቸው ፣እንደ ኔፍሊሞች አይደሉም። በተለይ ከዚህ ቫይረስ እንደ ዳነው ዊል ስሚዝ አይነት ሰዎችን ካገኙማ ነክሰው ወደ ህብረታቸው ይቀላቅሉታል፣ ነካሽ መናፍስቶች ብላቹ እንዳትገስፁ ደግሞ፣ ፊልም ነዋ። በፊልሙ ላይ የብቸኝነት ቋት ተከምሮበት የሚታየው ዊል ስሚዝ ከአንድ ውሻው ጋር ከወዲህ ወዲያ ይንገዋለላል። ውሻው ባያወራውም እሱ ግን ያናግረዋል፣ይዘፍንለታል። ደሞ እኮ “ዶንት ዎሪ” እያለ ነው ሚዘፍንለት። በውጭው ዓለም ለእንስሳ በተለይም ለውሻ ያላቸው ቦታ ከፍተኛ ቢሆንም በዚህ ፊልም ላይ ግን የዊልን የብቸኝነት ክፍተት ውሻው ሊሞላለት አልቻለም፣ለሰው ሰውን የሚያህል ፍጥረት የለምና ይመስለኛል። እኔስ በልጅነቴ “መቻል” የሚሉት ውሻ ካባረረኝ ወዲያ “እዚህ ግቢ ውሻ አለ?” ብዬ ጠይቄና የቦቢ ድምጽ አለመኖሩን አረጋግጬ ነው ምገባው፣ የውሻን ነገር ውሻ ያነሳዋል ብዬ ነው የነመቻልን ትዝታዬን የዶልኩት።

ወደ ፊልሙ እንመለስ እስኪ፣ ይህ ብቸኝነት ያናወዘው ጎበዝ፣ ሰዎች በሌሉበት ገበያ (ሱፐር ማርኬት) ሄዶ ዕቃ ይገዛል፣ ብቻውን ይገዛና ለብቻው ይከፍላል። እንደውም ከገበያው ውስጥ የሰው ምስያ መስለው ከተሰየሙት አሻንጉሊቶች ጋርም ያወራል። እናማ ይህ ሁሉ የአእምሮ ግጭት ሲፈጠር በደህና ጊዜ የነበሩትን ሚስቱና ልጆቹ በሃሳብ እየመጡ ያናውዙታል፣ ንፁህ ፍቅራቸው በህልም ቅዠት እየመጣ እየታየው ያሰቃየዋል። በነገራችን ላይ “ጥሩ” ነገር ካለፈ “መጥፎ” ትዝታ ይሆናል።

የጥይት መሳሪያውን ይጠጋግናል፣ ስፖርቱን ይሰራል። ዊልን አይቼ ይሆን ስፖርት የጀመርኩት? ምንም ሴፕስ(ጡንቻ) አይኑረኝ፣ ብቻ ቦርጭ አጥፍቻለው፣ ሃሃሃ። ብቸኛው ጎልማሳ በቫይረሱ የተጠቁት አውሬዎቹ መተው እንዳይነካክሱት የቤቱን በር እና መስኮት በደንብ ይከረችመዋል። ከዚህ በኃላ ምን ያደርጉለታል፣ ሰው መሆናቸው አብቅቷል።

የመጨረሻ መተንፈሻ የሆነውም ይህ ውሻ በቫይረሱ በተጠቁ ውሾች ተነክሶ ሞተበት። እናማ በጭንቀት ሊፈነዳ የደረሰው ዊል በቫይረስ የተበከሉትን የሰው ልጆች ወደ ሚመለሱበትና የሚፈወሱበት እውነት እንዲቀይራቸው ታገለ። እውነትም legend! ያለ ሰው እንደማይኖሩ አውቆ ሰውን መፈለግ ጀግንነት ካልሆነ ሌላ ምን ጀግንነት ሊሆን ይችላል? እዚህ ጋር ስለ ዊልና እሱ ስለሚተውንበት ፊልም ላብቃና ስለ ቅዱስ ጳውሎስ የተወሰነ ልናገር።

 

ቅዱስ ጳውሎስ

ይህ የጌታ ሐዋርያ ምንም ታላቅ ቢሆን የሰዉን እገዛ በመፈለግ እና ሰዎችን በመናፈቅ ጡዘት ውስጥ የገባበት ጊዜ ነበር። “በእናንተም መካከል ወደ መቄዶንያ እንዳልፍ ደግሞም ከመቄዶንያ ወደ እናንተ መጥቼ ወደ ይሁዳ በጉዞዬ እንድትረዱኝ አሰብሁ።” (2ኛ ቆሮንቶስ 1:16) “እንድትረዱኝ አሰብሁ”? ምንድነው ሐዋሪያው የሚለው? እርዳታ!?] ጳውሎስም እርዳታ ይፈልጋል? አዎን ሰው ነውና።

ሌላው ካጋጠመው ኃዘን ውስጥ አንዱ በሮማውያን አሰቃቂ የእስር ቤት ብቸኝነት እንደነበር ስለ አፍሮዲጡ ሕመም በተናገረው ጥቅስ ውስጥ እንመለከታለን። በሮም በአሰቃቂ እስር ውስጥ በነበረበት ወቅት፣ ጌታ ብቸኝነቱ አሳስቦት አፍሮዲጡን እንደፈወሰው ማየት ይቻላል በጥቅሱ። “በእውነት ታሞ ለሞት እንኳ ቀርቦ ነበርና፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ማረው፥ ኀዘን በኀዘን ላይ እንዳይጨመርብኝ ለእኔ ደግሞ እንጂ ለእርሱ ብቻ አይደለም።” (ፊልጵስዩስ 2: 27) “ኃዘን በኃዘን ላይ”፣ ሰው ያለ ሰው ኃዘን የሚደራረርበት ምስኪን ፍጥረት ነው። ሐዋርያው የአፍሮዲጡ መትረፍን አፅንዖት ሰጥቶ “ለእኔም ነው” ይላልና። በሌላም ክፍል “ላያቹ ናፍቄአለው” ይላል። እውነትም እንደ ሰው የሚናፈቅ የአምላክ ውድ ስጦታ አለም ላይ ምን ሊኖር ይችላል? ምንም!!

እንደ ዊል ስሚዝ አንድ ከተማ የሚሞላ ብቃት ቢኖረን፣. ያለ ሰው ብንኖር ከቅዠት አንተርፍም። እንደ ሐዋርያው ለብዙዎች የሚተርፍ ፀጋ ቢገለጥብን፣ ያለ ሰው ከኖርን መቼ እንደሚወድቅ የማያውቅ በአንካሴ የሚዘል ዓይነት ሰው እንሆናለን። ‘ያለሰው ቢወዱት ምን ያደርጋል አገር’ ብሎም አልነበር በአሉ ግርማ ኦሮማይ ላይ።

በመጀመሪያ በሰዎች ለመከበብ መፍጠን የለብንም፣ እሱም የራሱን የቻለ አደጋ አለውና። አስቀድመን ለሌሎች ሰው መሆን እንድንችል ነው መፀለይ ያለብን። ይህ እውነትም ገብቶን እንንቀሳቀስ። ያኔ አንድ ከተማ የሚፈውስ ኃይል ከጌታ ዘንድ እናገኛለን። “ጌታ በህዝቡ ዙሪያ ነው”፣ ሰዎችን ጥሎ አየር ላይ የሚበር አምላክ የለን ይላልና ቃሉ።

በሌላም ክፍል “ላያቹ ናፍቄአለው” ይላል። እውነትም እንደ ሰው የሚናፈቅ የአምላክ ውድ ስጦታ አለም ላይ ምን ሊኖር ይችላል? ምንም!!

 

መዝጊያ

እንደ ዊል አንድ ከተማ የሚሞላ ብቃት ቢኖረን፣. ያለ ሰው ብንኖር ከቅዠት አንተርፍም። እንደ ሐዋርያው ለብዙዎች የሚተርፍ ፀጋ ቢገለጥብን፣ ያለ ሰው ከኖርን መቼ እንደሚወድቅ የማያውቅ በአንካሴ የሚዘል ዓይነት ሰው እንሆናለን። ‘ያለሰው ቢወዱት ምን ያደርጋል አገር’ ብሎም አልነበር በአሉ ግርማ ኦሮማይ ላይ።

በመጀመሪያ በሰዎች ለመከበብ መፍጠን የለብንም፣ እሱም የራሱን የቻለ አደጋ አለውና። አስቀድመን ለሌሎች ሰው መሆን እንድንችል ነው መፀለይ ያለብን። ይህ እውነትም ገብቶን እንንቀሳቀስ። ያኔ አንድ ከተማ የሚፈውስ ኃይል ከጌታ ዘንድ እናገኛለን። “ጌታ በህዝቡ ዙሪያ ነው”፣ ሰዎችን ጥሎ አየር ላይ የሚበር አምላክ የለንማ ስለዚህ ያለ እግዚአብሔር እና ያለ ሰው መንፈሳዊነትን ማሰብ የለብንም። ሁሌም ለእግዚአብሔር የሚኖር ሰው ሰዎችን ለማዳን ይሮጣል።

ለክርስቲያን ኑሮ ማለት ከአምላኩ ጋር ሕብረት እያደረገ ባልንጀራውን እንደ ራሱ እየወደደ መኖር ማለት ነው። ሰውን መውደድ፣ ለባልንጀራ መቆረስና ህይወትን ሳይሳሱ ለወዳጅ መስጠት ለሰው መኖር በሚለው ትርጉም ውስጥ በጉልህ መቀመጥ አለባቸው። ባልንጀራን መውደድ አምላኩን ከሚወድ አማኝ ይጠበቃል። ጌታችን ያለምክንያት አይመስለኝም የደጉ ሳምራዊን ምሳሌ የነገረን።

ዊል ብቻውን ከሚኖር ወደ አውሬነት የተለወጡትን ወደ ሰውነት ለመለወጥ ታገለ፣መፈወሻ መንገድ ለማግኘት ባተለ።አንድ ከተማ የሌላትን አንድ ሰው አለውና። ሐዋርያው ያለ ሰው እንደማይችል አውቆ “እንድትረዱኝ አሰብኩ” አለ። ከሰው ጋር ለመኖር እና ሰዎችን ለማዳን የሚታገል ሁሌም የእግዚአብሔር “legend” ይባላል።

ሐምሌ፣ 2009

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

x

Check Also

Fikadu Borena Week Four

Related

%d bloggers like this: