Home » Articles » ሐሰተኞችን እስከምን ድረስ እንታገሳቸው?

ሐሰተኞችን እስከምን ድረስ እንታገሳቸው?

ክፍል ሁለት

ፍጹማን ግርማ

በመጀመሪው “ሐሰተኞችን እስከምን ድረስ እንታገሳቸው?” በሚል ርዕስ በተጻፈው ጽሁፍ ውስጥ፣ የሳቱትን አገልጋዩች ለመከላከል በሚል በተደጋጋሚ ከሚጠቀሱ ጥቅሶችና አመለካከቶች የተወሰኑትን ለማየት ሞክረን ነበር። የተጠቀሱትን ሁለቱን ነጥቦች ለማስታወስ ያክል፡-

1-” እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ”

2- “ሐሰተኞችን ስማቸው ሳይጠቀስ በደፈናው እንቃወም” የሚሉ ነበሩ

በዚህ ጽሁፍ ከተለመዱት የመከላከያ አባባሎች ሶስተኛውን እንመለከታለን።

3- “እኔ የሃሰት አስተምህሮንና ልምምድ የመለየት ፀጋው አልተሰጠኝም፤ ስለዚህ የኔ ድርሻ አይደለም”

እነዚህ ወገኖች የሐሰትን ትምህርትና ልምምድ እንደቃሉ ሚዛን መለየትና አስፈላጊውን ዓይነት ራስን የመከላከል ብሎም ሌላውን ምእመን ማሳወቅ ግዴታቸው የማይመስላቸው ሰዎች ናቸው። “ውስጡን ለቄስ” በሚል ለራሳቸው የፈለጉትን ካገኙ ስለሌላው ምን ያስጨንቀኛል የሚሉ ግደሌሽነትም ይታይባቸዋል። በአመዛኙ ሲታዩ በእግዚአሔር ስም የተነገረን ነገር መመርመርና መፈተሽ ድፍረት የሚመስላቸው፤ አልፎ ተርፎ የእግዚአብሔር መቅሰፍት ያገኘኛል ብለው የሚፈሩ ናቸው።

 

“የመለየት የፀጋ ስጦታ አልተሰጠኝም” ማለት የራስ ህሊናን ማሞኘት ነው። ቢያንስ ሐዋሪያው ጳውሎስ በ1ተሰ 5፥21 “ሁሉን ፈትኑ…ሁሉንም መርምሩ” ብሎ ሲጽፍ ወይም ሐዋሪያው ዩሐንስ “ወዳጆች ሆይ መንፈስን ሁሉ አትመኑ”(1ዩሐ 4፥1) ሲለን ፤ የመጽሐፉን ገጽ ለመሙላት ቃላት እያሰማመሩ እንዳይደለ ግልጽ ነው። ይልቁንስ የመፈተንና የመለየት ተግባር በሁሉም አማኝ እንዲከናወን ሲያስተምሩና ሲያስጠነቅቁ እናስተውላለን። መልዕክትን የመለየት ግዴታ የሁሉም የሰሚዎች መሆኑን አንዘንጋ። በእግዚአብሔር ስም ተናግሯል በሚል ሳንመረምር እንመን የሚለው ቅኝት እግዚአብሔርር የማይቀበለው ሞኝነት ነው። ስለዚህ እንመረምራለን ደግሞም እናምናለን።

 

“የፀሎት-የንግድ ቤት?” በሚል በቅርብ በታተመው መጽሐፋቸው ወንድም ተካልኝ ነጋ እንዲህ አስነብቦናል። “ትክክልን ከሐሰት መለየት በእርግጥ ቀላል አይደለም። እንድንለይ በመንፈሳዊ ሕይወታችን ልንደረጅ እንብሰል፤ መለየት ከመንፈሳዊ ብስለት ጋር ትስስር አለውና!…”ጠንካራ ምግብ ግን መልካሙንና ክፉውን ለመለየት በሥራቸው የለመደ ልቡና ላላቸው ለፍጹማን ሰዎች ነው።”(ዕብ 5፥11)። ካስተዋልን በስሙ ለሚመጡ መታለሎች የሚጋለጡ፣ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ብስለት የሌላቸው መሆናቸውን እንገነዘባለን። የቤሪያ ሰዎችም የተመሰከረላቸውና ምስጋናን የተቀበሉት፣ የተባሉትን ስለተቀበሉ ብቻ ሳይሆን ነገሩ እንዲህ ይሆንን በሚል መንፈስ ከመቅረባቸው የተነሳ መሆኑን አንርሳ (ሐዋ 17፥11)። ነገርን መመርመር ቸልተኝነት ወይም አለማመን ሳይሆን ለሰማነው ነገር ያለንን ክብር የሚያመለክት መሆኑን እንወቅ።”

 

ለቆሮንቶስ አማኞችም ሐዋርያው ስጽፍ ማንኛውም ትንቢት በጉባዔው ሲነገር፤ ሌሎች የሚለዩ ሰዎች ጉዳዩን ይለዩት፣ ይመርምሩት ተብሎ ተጽፏል። ዛሬ ዛሬ ግን ነቢያት እንደ አሸን በፈሉበትና ሁሉም እንደወደደው ለስም በሚሻማበት ወቅት ፤ ቤተ ክርስቲያን ምን ያክል የሚነገረውን ትንቢት የሚለዩ ሰዎችን እንዳሰማራች ቤት ይቁጠረው።

 

እንደ ቃሉ መሰረት መሆን የነበረበት ከነቢይነት አገልግሎት ጋር የመለየትም ስራ አብሮ መቀጠል ያለበት ጉዳይ ነበር። ምክንያቱም የፀጋ ስጦታው ካለው አስቸጋሪ ባህሪይው በመነሳት ሁለቱ ስራዎች አይነጣጠሉም። በርግጥ እንዲህ ተደርጎ ቢሆን ኖሮ በየሚዲያውም ሾልከው የሚወጡ ትንቢት መሳይ እንቶ-ፈንቶዎች የጌታን ስም ባላስነቀፉ፤ የየዋህ አማኞችንም ልብ ባልሰበሩ፤ በኢ-አማኒያን ዘንድ አንገት ባላስደፉን ነበር።

 

መመርመር አለብን ከተባለ ዘንዳ፣ ታዲያ እንዴት እንመረምራለን? የሚለው በጣም ተገቢ ጥያቄ ይሆናል።

በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአውሮፓ በተቀጣጠለው የተሃድሶ እንቅስቃሴ ወቅት እነ ማርቲን ሉተር ዋናው መፈክራቸው… “sola scriptura!”…(መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ!)…የሚል ነበር። ይህም በቤተክርስቲያን ውስጥ ማንኛው ግለሰብ፣ አስተምህሮም ሆነ ልምምድ ለቃሉ ስልጣን መገዛት አለባቸው፤ በማንኛውም ጉዳይ ቃሉ የመጨረሻ ቀያጅ ባለስልጣን ነው የሚል ነበር።

 

ስለዚህ ማንኛውም ትንቢትም፣ትምህርት ሆነ እነሱን ያመጧቸው ነቢያት ወይም አስተማሪዎች፤ ክቡር በሆነው በቃሉ ቱምቢ ይመዘናሉ፣ ይፈተሻሉ። በቃሉ ሚዛን ቀልለው ከተገኙ ውድቅ እንደርጋለን፣ አንቀበልም ፤ ጤናማና ቃሉን የሚደግፍ ሲሆን ብቻ እንቀበላለን፣ ለተግባራዊነቱም እንንቀሳቀሳለን።

 

አንዳንዶቹ ነቢያት እንደሚያስፈራሩት ሁሉንም ንግርታቸውን እንደወረደ ባለመቀበላችን የሚደርስብን ምንም አይነት ቅንጣት መቅሰፍትም ሆነ የሚያመልጠን በረከት እንደማይኖር መጽሐፍ ቅዱስ ምስክራችን ነው! (ዘዳ 18፥22)…ደግሞም ቅዱሳት መጽሐፍት ያስፈራሩንን ሁሉ እንድንፈራ አያዙንም። እንዲያውም ምሳ 26፥2 ላይ “…ከንቱ እርግማን በማንም ላይ አይደርስም” ብሎ ያስረግጥልናል። አንዳንድ የዋህ አማኞች ግን ፍርሃታቸው ሲታይ እነሱ ለእግዚአብሔር የእንጀራ ልጅ የሆኑ ይመስላቸዋል። ነገር ግን በፍጹም አይደለም። እግዚአብሄር የእንጀራ ልጅ የለውም። በትክክለኛ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምክንያት ያልተመሰረተ ንግግር በሕይወታችን ላይ ምንም አይነት ተጽዕኖ ሊያመጣ አይችልም።

 

ከላይ በተጠቀሰው መጽሐፋቸው ጸሐፊው ወንድም ተካልኝ…”ክርስቲያናዊ ፍርሀት የሚመነጨው እግዚአብሔርን ከመፍራት እንጂ ከሌላ አይመነጭም።…ሐሰተኛ ነቢያት በፍርሃት አቂላችንን አጥተን በጭፍን በሚያሳዩን መንገድ እንድንጠበጥብ ሥነ ልቦናዊ ጫና ያሳድራሉ።…ድፍረቱ ከእግዚአብሔር ጋር ለወገነው ለኛ መሆን የነበረበትን ሥርዓት ያቃውሳሉ። እውነትን በፍርሃት ጠፍንጎ ሐሰት ያለ ከልካይ እንዲፋንን መንገድ የከፈተው የክርስቲያናዊ ብስለት በጉባኤዎቻችን መታጣቱ ነው።” ብለዋል።

 

ስለዚህ ለአማኞች ከአገልግሎትም በፊት ቃሉን ማወቅና ማጥናት ፤ በቃሉ እውነት መተከል እጅግ አስፈላጊ ይሆናል ማለት ነው። በመካከላችን ያለው የስላሴ አንዱ አካልና ራሱ አምላክ የሆነው መንፈስ ቅዱስም በቃሉ እውነት ላይ ተመርኩዞ ማረጋገጫዎችን እየሰጠን ወደ እውነት ሁሉ ይመራናል።

– (ይቀጥላል)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

x

Check Also

Fikadu Borena Week Four

Related

%d bloggers like this: