Home » Articles » ሐሰተኞችን እስከምን ድረስ እንታገሳቸው?

ሐሰተኞችን እስከምን ድረስ እንታገሳቸው?

ክፍል አንድ

ፍጹማን ግርማ

 

የክርስቶስን ወንጌል ሰባኪዎች እንዳሉ ሁሉ ልዩ ወንጌል ሰባኪዎችም አሉ፤ እውነተኛ ነቢያት እንዳሉ ሁሉ ሐሰተኛ ነቢያትም አሉ፤ እውነተኛ አስተማሪዎች እንዳሉ ሁሉ ሐሰተኛ አስተማሪዎችም አሉ። በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትልቅ ፈተና ከሆኑት መካከል የስሕተት ትምህርትና እንግዳ ልምምዶች መሆናቸው ተደጋግሞ በመነገር ላይ ያሉ አሳሳቢ ጉዳዮች ናቸው። ባለፉት ዓመታት የኑፋቄ ትምህርቶችና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ይዘት የጎደላቸው ልምምዶች የአብያተ ክርስቲያናት ደጆችን ሲያንኳኩ ከርመዋል። በአንዳንድ ቦታዎች ላይም ተሳክቶላቸው ደጅ አስከፍተው ወደ ውስጥ  መዝለቅ ችለው ነበር። ይህም እንኳ ሆኖ ከሞላ ጎደል በአብያተ ክርስቲያናት መካከል ተመሳሳይ የወንጌል መልእክት ይተላለፍ ነበር ማለት ይቻላል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን፣ በተለይም ከኤሌክትሮኒክ ሚዲያው መምጣት ጋር ተያይዞ የስሕተት ትምህርቶቹ የቤተ ክርስቲያንን ደጅ ከማንኳኳት ይልቅ በቴክኖሎጂው ድጋፍ በቀጥታ ወደ አማኞች ቤት መዝለቅ ችለዋል። በዚህም አማኞች የትም ሳይሄዱ፣ ቤታቸው ቁጭ ብለው ከትምህርቶቹ ጋር የመተዋወቅ “ዕድሉ” ተፈጠረላቸው።

 

በድህረ-ነፃነት ማግስት በተለያዩ የወንጌላውያን አማኞች ምስባኮች ላይ ሳይታወቁ ሾልከው ገብተው እየናኙ ከመጡት ሐሳዊ አስተምህሮዎችና የተዛነፉ ልምምዶች “አማኞችን” ተጠንቀቁና ተጠበቁ ተብሎ ሲመከር እንሰማለን። የወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረትም በቅርቡ ያወጣው የአቋም መግለጫ የዚሁ ምክር ዋና ማሳያ ነው።

 

ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ ቤተክርስትያን ውስጥ የሚታዩ ስህተቶችን የሚያስጠነቅቁ ግለሰቦችና ህብረቱንም ጭምር ኢላማ ያደረጉ የተለያዩ ትችቶች ከእኛው ከአማኞች ሲደመጥ ይስተዋላል። አንዳንዴ ዱላ ቀረሽ የሚባል የቃላት ፍትጊያና መወራወር በሁለቱ ጎራዎች መካከል በተለያዩ መድረኮችና ማህበራዊ ሚዲያዎች መመልከት የተለመደ ሆኗል።

 

አሁን ያለው ሁኔታ የተመቻቸውን ሰዎችን በሁለት ጎራ ከፍሎ ማየት ይቻላል። የመጀመሪያዎቹ (በጸሐፊው እይታ አብዛኛዎቹ) የነገሩ አሳሳቢነት ብዙም ያልመሰላቸው ለዘብተኞች ናቸው። እነዚህ ሰዎች አሁን እዚህም እዚያም የሚታየውን የግርግር እንቅስቃሴ ለኢትዩጵያ በተገባላት የተስፋ ቃል መሰረት የመጣ “ሪቫይቫል” ነው ብለው የሚያምኑና ችግሮችን እየተመለከቱም በየዋህነት የቤት “ገመና” እንዴት እውጪ ይሰጣል ዓይነት የማምለጫ ምክንያቶችን እየሰጡ የሚሄዱ ናቸው። ሌሎቹ ደግሞ የስህተት አስተምህሮዎችና ልምምዶች ዋና መሪ ወይም አጋፋሪ በመሆን ምዕመኑን የሚበዘብዙና የሚያደናግሩ፤ ምንም ዓይነት ጥያቄ ሲነሳ ገመናቸው ተጋልጦ በግል ጥቅማቸው (ሃብት፥ስም፥ ዝና) ላይ ስለሚመጣባቸው በክፉ መሰሪነት ተነስተው ጥያቄዎቹን ለማፈን የተዘጋጁ ናቸው። ለዚህም ክፋታቸው ማስፈጸሚያ የማይፈነቅሉት ዲንጋይ የለም።

 

ይህ ጽሑፍ በሁለተኛው ጎራ ለተሰለፉት “ደፋር” ሰዎች ፋይዳው ብዙ እንደማይሆን ግልጽ ነው። “አውቆ የተኛን…” አይነት ምላሽም ከነሱ የተጠበቀ ነው። ነገር ግን የለዘብተኛና የዋሆችን አቁዋም ግን በትንሹም ቢሆን እንደሚሞግትና፣ በመሃል ቤት ሆነው የተፍገመገሙትንም ያፀናል የሚል እምነት አለኝ።

 

እንደሚታወቀው ሐሳዊ አስተማሪዎች ለስህተታቸው ከቅዱስ ቃሉ በጥራዝ ነጠቅ መልኩ እንደሚጠቅሱት ሁሉ እነዚህም  ሰዎች አትቃወሟቸው ለማለትም ከቃሉ ይጠቅሳሉ። ድሮስ የስህተት ትምህርት ትልቁ ክፋቱ ሙሉ በሙሉ ሃሰት አለመሆኑም አይደል?

እስኪ የሳቱትን ለመከላከል በተደጋጋሚ ከሚጠቀሱ ጥቅሶችና አመለካከቶች የተወሰኑትን ከሞላ ጎደል እንመልከታቸው።

 

1–” እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ፤ በምትፈርዱበት ፍርድ ይፈረድባችኋልና (ማቴ 7፥1-2)

መቸስ ይኸ ጥቅስ ከዓውዳቸው ውጪ ያለትርጉማቸው ለተሳሳተ ዓላማ ከሚውሉት ጥቅሶች ግንባር ቀደሙ ሳይሆን አይቀርም። ይሁንና በዓውዱ ውስጥ ምዕራፉን ዘልቀን ስናነበው ጌታችን ኢየሱስ እያስጠነቀቀ የነበረው ግብረ-ገብነት ላይ ያተኮረ የግብዝነት ወይም የአስመሳይነት ፍርድ ነበር። ይህም ሲባል እኛ የማናደርገውን የማንፈጽመውን ተመሳሳይ እኩይ ተግባር ሌሎች ላይ ድክመት ሆኖ ስንመለከት፣ ጥፋተኛነታቸውን በማጉላት ጣት መቀሰር ልክ አለመሆኑን ያመለክተናል።

 

ነገር ግን አንድ ግለሰብ ወይም ማህበር በታወቁ ኑፋቄያዊ ስህተቶች ውስጥ ከወደቁ ስህተቱ ላይ መፍረድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው። ከቀደሙት ሐዋርያትም የተማርነው እውነት ይህንኑ የሚደግፍ ነው።ሐዋርያው ጳውሎስ ለገላትያ አማኞች …”ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ፥ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ፥ የተረገመ ይሁን።” ሲል… በራሱና በመላእክትም ጭምር የ’ርግማን ፍርድ ያውጃል። ታዲያ ለአንድ ሰው በራስ ላይ ጨክኖ ከመፍረድ በላይ የሆነ ፍርድ የታለ?

 

በመጀመሪያውና ክፍለ ዘመንና ቀጥሎም የነበረችው የጥንቷ ቤተክርስቲያን አባቶች ስህተትን “ስህተት ነው” እያሉ ባይፈርዱና ባያወግዙ ኖሮ፤ በስህተት አስተምህሮች ላይ ተደጋጋሚ ጉባዔዎችን በየጊዜው ባያደርጉ ኖሮ፤ ይኸ ንጹህ ወንጌል ዛሬ በእኛ ዘመን እንዴት ሊደርሰን እንደሚችል ማሰብ ይከብዳል።

 

ስለዚህ “አትፍረዱ” የሚሉት ለዘብተኛ አማኞች ቃሉን በተሳሳተ አውድ ተርጉመውት ካልሆነ በስተቀር የወንጌል እውነት ጸንቶ እንድኖር ቅዱስ ቃሉን መሰረት አድርገን በቅን መንፈስ ሐሳዊ ትምህርቱ ላይ እንዴት አንፈርድም? እንፈርዳለን እንጂ! ካስፈለገ በራሳችንና  በመላዕክትም ጭምር።

 

ማንም አማኝ የትኛውንም ትምህርት ወይም ልምምድ በቃሉ ቱምቢ ፈትኖና፣ ፈትሾ ወደ እውነት የሚመራውን ቅዱሱን መንፈስ አድምጦ፣ መልካም የሆነውን እንዲይዙ መጽሐፉ ያዛልና።

 

2– “የግለሰቦችን ሥም ሳንጠራ፥ በደፈናው ብናወግዝስ?” የሚል አመለካከት

እነዚህኞቹ ደግሞ ስህተትን በመፍረድ ወይም በማውገዝ ያምኑና፤ የግለሰቦችን ሥም በይፋ እየጠሩ ከማስጠንቀቅ ይልቅ አስምህሯቸውን ብቻ በደፈናው መቃወም አለብን ይላሉ። ይህ ሃሳብ ከላይ ከላይ ሲታይ ቅቡልና ክርስቲያናዊ “ጨዋነትን” የተላበሰ ይመስላል።

 

ነገር ግን ለዚህ ዓይነት ምልከታ ምንም ዓይነት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ አናገኝም። መጽሐፍ ቅዱስ (በተለይም አዲስ ኪዳን) የሳቱ አስተማሪዎችን በስም እየጠሩ፣ የስህተት አስተምህሮዎችንና የተዛነፉ ልምምዶችን በምሳሌያዊ ማብራሪያ ጭምር እያስደገፉ በሚያወግዙ ምንባባት የተሞላ መጽሐፍ ነው።

 

ሐዋሪያው ጳውሎስ በተደጋጋሚ በመልዕክቶቹ ውስጥ የሃሰተኞችን ስም ከነስህተት አስተምህሯቸው ዓይነት ጋር እያብራራ ያለመታከት ይጽፍ ነበር። በተጨማሪ የይሁዳንና የጴጥሮስንም መልዕክቶችንም ማንሳት ይቻላል። ሐዋርያቱ ሲቃወሙ ሃሰተኞቹ በግልጽ የሚያስተምሩትን ስህተት በግላጭ ሥም ጠርተው ይቃወማሉ እንጂ ጠቅላላ ትምህርት ብቻ አልሰጡም። ይኸው ከዚያ ዘመን አልፎ ተርፎ አሁን ለእኛም ትምህርት እንዲሆኑልን ዘመናትን በሚሻገር መጽሐፍ ተጽፈው ዛሬም ድረስ አሉልን።

 

ስለዚህ መሰረታዊ የክርስትና አዕማድ አስተምህሮዎች ላይ ከመጽሐፍ ቅዱስ የወጣ አስተምህሮ ሲቀርብ ፣ “ሌላ” ኢየሱስ ሲሰበክ ፣ ሐዋሪያት ያልሰበኩት ልዩ ወንጌል መድረክ አግኝቶ ሲደመጥ ስናይ ለወንጌል እውነት ወግነን ደማቅ የልዩነት መስመር ማስመር የግድ ይላል። በለሆሳስ አናወግዝም። በገደምዳሜው አንሸፋፍንም።

 

ምክንያቱም  ይኸ ጭንቁር ትምህርታቸውና ራሳቸው አስተማሪዎቹ በተሸሸጉና በደበቅናቸው ቁጥር መርዛማ ትምህርታቸው እየበዛ የሚሄድ “እርሾ” ስለሆነ ብዙ ምስኪን ንጹሐንን እንዳያቦካና እንዳይዛመት በማሰብ ነው። አለፍ ሲል ደግሞ ጉዳዩ ተራ የሥነ-መለኮት ጉንጭ አልፋ ክርክር ሳይሆን የመዳንና ያለመዳን ፤ የእግዚአብሔር ወይም የሰው አገልጋይ የመሆን ጥያቄ ይሆናልና ነው፡፡

 

ሌላው መዘንጋት የሌለበት ጉዳይ፣ ይህን ሁሉ ስናደርግ ሉዓላዊና አዶናይ የሆነው እግዚአብሔር የኛ ጠበቃነት የግድ አስፈልጎት አይደለም። ይልቁንስ በብዙ ስደትና መከራ ለኛ የደረሰንን የወንጌል አደራ ሳይሸቀጥ ለቀጣዩ ተረካቢ ለማስረከብ የራሳችንን ኢሚንት  ድርሻ ለመወጣት ያክል እንጂ። እኛ ወደድንም ጠላን እርሱ እውነትን ብቻውን ለዘላለም የሚጠብቅ አምላክ ነው። ዝም ብንልና የሚገባንን ባናደርግ ግን ክንዱ ከሌላ ምንጭ መዳንን ታመጣለታለች። እኛስ ምን ይተርፈናል ካልን? መለኮታዊ “ትዝብት” ብቻ ይሆናል።

 

የነገረ ክርስቶስን (Christology) አስተምህሮ የሚያጣምም፣ በክርስቶስ ውድ የደም ዋጋ የተገኘን የአማኙን ደኅንነትን ለማስጣል ከመስቀሉ ላይ ዓይኑን እንዲያነሳ በማድረግ አደጋ ውስጥ የሚጥል አዚማዊ ትምህርት በግልጽ በአደባባይ እየተስተማረ ዝም ተብሎ ሲበቃ፤ የሃሰተኛ አስተማሪዎች ስም ተጠርቶ መወገዙን፣ ትምህርቱና ልምምዱ መተቸቱ ሲታይ አጉል መቆርቆር ምን የሚሉት “ትህትና” ነው? በአደባባይ ማይክ ይዞ፣ የቲቪ ቻናል ተከራይቶ፣ ስም ጠርቶ  “ሰይጥኗል” ተብሎ ሲሰበክ ምንም ሳይባል፤ የሃሰተኛ አስተማሪዎችን ስም አትጥሩ ብሎ ማለባበስ ለማንስ ይበጃል? (ሐዋሪያው ጳውሎስ እንዳለው …ማንን ነው የምናስደስተው? ሰውን ወይስ እግዚአብሔርን?)

(ይቀጥላል) …..

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

x

Check Also

Fikadu Borena Week Four

Related

%d bloggers like this: