Home » Articles » ሰው፣ ኃጢአትና የእግዚአብሄር መፍትሄ

ሰው፣ ኃጢአትና የእግዚአብሄር መፍትሄ

በአሌክስ ዘፀአት

 

የኃጥአትና የኃጥተኝነት ምንጩ የስነ-ምግባር ችግር አይደም ፣ የወረስነው ዘር (Sin Seed) እንጂ፡፡  በስነ-መለኮት የመጀመሪያው ኃጢአት (Orgional Sin) የሚባል ነገር አለ፡፡ ያ ኃጢአት የሰው ሁሉ አባት የሆነው አዳም ያደረገው የመጀመሪያ ኃጢአት ነው፡፡ አዳም በዲያብሎስ በተታለለና የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ በተላለፈ ጊዜ ወደ ማንነቱ ውስጥ የአመጽ ዘር ገባበት፡፡ እንደ ሐዋሪያው ቅዱስ ዮሐንስ ገለጻ ከሆነ ኃጢአት የተጀመረው በአመጽ ነው፡፡ “አመጽ ኃጢአት ነው፡፡” (1ዮሐንስ 3 ፡ 4) ያ በሰው ልጆች ታሪክ የመጀመሪያ ኃጢአት ነው፡፡ “የመጀመሪያዎቹ ወንድና ሴት ከእግዚአብሔር ጋር በቀጥታ መነጋገር ይችሉ ነበር ይሉና ፤ ነገር ግን ከፍጥረታት ሁሉ መካከል በእግዚአብሔር ላይ የማመጽ ነፃነት ያላቸው እነዚሁ ሰዎች ነበሩ” ይላሉ ፊልፕ ያንሴ፡፡ (ቅይማት ገጽ 110) እንደ እውነቱ ከሆነ ደግሞ አመጽ የተጀመረው በገነት መካከል በአዳም አማካኝነት ሳይሆን በብርሃኑ መልአክ በሉሲፈር አማካኝነት በሰማይ በእግዚአብሔር ዘንድ ነው፡፡ (ትንቢተ ኢሳይያስ 14 ፡ 12-17 ፤ ትንቢተ ሕዝቅኤል 28 ፡ 12-19) እዚያ የተካሄደው መፈንቅለ-መንግስት መሰል ሴራ ወይም አመጽ ነበር፡፡ ለዚህም ነው ሐዋሪያው ቅዱስ ዮሐንስ “…ዲብሎስ  ከመጀመሪያው ኃጢአትን ያደርጋልና” ( 1ዮሐንስ 3 ፡ 8) ያለው፡፡ ሰይጣን ያን አመጽ ነበር በኤደን ገነት ለመጀመሪያው ሰው ያጋባው፡፡ ሐዋሪያው ቅዱስ ጳውሎስ “ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ ይላል ፤ ቀጥሎም በአዳም መተላለፍ ምሳሌ ኃጢአትን ባልሰሩት ላይ እንኳ ሞት ነገሰ … አዳም ይመጣ አንድ ላለው ለእርሱ አምሳሉ ነውና” (ሮሜ 5 ፡12-14) ይለናል፡፡ ልክ ሌዊ ገና ሳይወለድ በአብርሃም ወገብ ውስጥ ሆኖ እጁን ዘርግቶ ለመልከጼዴቅ አስራትን እንደሰጠ (ዕብራውያን 7፡4-10) ፤ ከአዳም ቀጥሎ ከአዳም የሚመጣ ሰው ሁሉ ገና ሳይመጣ በአዳም ወገብ ወስጥ ሆኖ አጁን ዘርግቶ በለስቱን በመብላት በመተላለፍ ወድቋል፡፡ ለዚህም ይመስላል ዘማሪ ዳዊት  “እነሆ በአመጻ ተጸነስሁ ፤ እናቴም በኃጢአት ወለደችኝ” (መዝሙረ ዳዊት 51፤5) ያለው፡፡ ሕፃን ሲወለድ ከድርጊት ውጤት ከተከማቸ ኃጢአት ጋር አይወለድም፡፡ ሕግ በሌለበት የህግ መተላለፍ የለም፡፡ የሕግ መተላለፍ በሌለበት ኃጢአት አይቆጠርም፡፡ ሕፃኑም ተወልዶ በእግዚአብሔር ሕግ ላይ በማመጽ ተላልፎ ኃጢአት ባላደረገበት ደረጃ ኃጢአተኛ የሚሆንበት አግባብ የለም ፣ ሲወለድ ከአባቱ አዳም በውርስ ያገኘውን የአመጽ ወይም ኃጢአት ዘር ይዞ ካልተወለደ በቀር፡፡ በመሆኑም ይመስላል መልካም ሆነ ክፉ ፣ እኩይ ሆነ ሰናይ የማያውቅ ሕጻን እንኳ ገና ከመዳሁ ብርጭቆ በመስበር አመጽ የሚጀምረው፡፡

 

ኃጢአት የተባለው ነገር ያስከተለው መዘዝ ከእግዚአብሄር መለየትና ከገነት መባረርን ብቻ አይደለም፡፡ ይህ በመተላለፉ ምክኒያት ከእግዚአብሔር የተለየ ሰው በየተኛውም መልኩ ወደዚህ ስፍራ መመለስ የሚስችል አቅም የለውም፡፡ ከሰው የሆነ የትኛውም ተግባር ይህን ሰው ወደዚያ ስፍራ መመለስ አይችልም፡፡ ይህ “ሰው በብልቶቹ መካከል በሚሰራ የኃጢአት ሕግ የሚመራ” (ሮሜ 7፡23) ፣ “ከኃጢአት በታች ሊሆን ለስጋ የተሸጠ” (ሮሜ 7፡14) ፣ “መልካም የማድረግ (ፈቃድ) ምኞት ያለው በተግባር ግን መልካም የማድረግ አቅም የሌለው” (ሮሜ 7፡18) “እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ ፣ ለዚህ ሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል?” እያለ ዘወትር የሚዋትት (ሮሜ 7፤24) አቅም አልባ ሰው ነው፡፡

ከኃጢአት ጋር በተያያዘ ሊታወቅ የሚገባው ሌላው ነገር የእግዚአብሄር የጽድቅ ፍላጎትና ባህርይ ነው፡፡ ከኃጢአትና ኃጢአተኛ ጋር ተያይዞ የእግዚአብሄር ጥያቄ ኃጢአት ያለማድረግ ብቻ አይደለም ፤ የፍትህ ጉዳይ ያለበትም ጭምር ነው፡፡ “የኃጢአት ደመወዝ (ዋጋው) ሞት ነው፡፡” (ሮሜ 6፡23) ኃጢአት ያደረገች ነፍስ መሞት አለባት፡፡ ይህ የእግዚአብሔር ፍርድ ነው፡፡ በመሆኑም የሰዎች በራሳቸው የስ-ምግባር መሻሻል ኃጢአት ያለማድረግና ሰናይ መሆን የእግዚአብሔርን የፍትህ ጥማት አያረካውም፡፡ ጥያቄው የነፍስ ነው ፣ ኃጢአት ያደረገች ነፍስ መሞት አለባት፡፡

 

የእግዚአብሔር መፍትሔ

ከላይ ለተገለጸው ሞት ለተፈረደበት ተስፋ የሌለው ኃጢአተኛ በብሉይ ኪዳን በእስራኤላውን ዘመን እግዚአብሔር ያዘጋጀው ጊዜያዊ መፍትሔ ነበር፡፡ አንድ ሞት የተገባው ኃጢአት ደረገ ሰው ነውር የማያውቅ የመስዋዕት እንስሳ ይዞ ወደ ቤተመቅደሱ ይቀርባል፡፡ ይሄ ሰው ሟች እንደሆነ የታወቀ ነው፡፡ እግዚአብሔር ይከሰዋል ፣ ሕጉ ፈርዶበታል ፣ ሕዝቡ ሁሉ ለመውገር ተዘጋጅቷል ፣ በእግአብሔርና በሰው ፊት በድፍረት እንድቆም የሚያስችል ህሊና የለውም፡፡ በመሆኑም ይህ መሞት የተገባው ኃጢአተኛ ሕዝቡ ሁሉ ባለበት እንስሳውን ይዞ ይቀርባል፡፡ ኃጢአተኛውም እጁን በጉ ላይ ይጭናል ፣ ካህኑም ሲጸልይ የግለሰቡ ኃጢአት ወደ እንስሳው ይተላለፋል፡፡ በዚያው ቅጽበት የእግዚአብሄር ትኩረት ከሰውዬው ወደ እንስሳው ይዞረል፡፡ ኃጢአቱን ተሸክሟልና መሞት እንዳለበት ይከሰሳል፡፡ ወዲውም እንስሳው ይታረድና ደም ይፈሳል፡፡ ነፍስ ደም ውስጥ ነውና ደሙ ስፈስ በእንስሳው ደም ኃጢአተኛው ምህረት አግኝቶ በነጻ ወደ ቤቱ ይሄዳል፡፡ ያም ስርአት ከእግዚአብሔር ዘንድ የኃጢአት ስርየትን ፣ ከማህበረሰቡ ከሞት ፍርድ ነፃ ማውጣትን ፣ ከራሱ ህሊና ክስ መዳንን ያመጣለታል፡፡

 

ከላይ የተገለጸው መፍትሔ ጊዜያዊ ነው ፤ ቢበዛ ለአንድ አመት ብቻ ዋስትና የሚሰጥ፡፡ እግዚአብሄር ከህግ ቀንበር ፣ ከኃጢአት ኃይል ነፃ ወጥተን የጽድቅ ኑሮ መኖር የምንችልበትን መፍትሔ አዘጋጅቷል፡፡

 

የወደቀው ፣ የተበላሸው ፣ የእግዚአብሔርን የጽድቅ ጥማት ማርካት ያቃተው ሰው ነው፡፡ ሰው ያበላሸውን ሰው ማስተካከል አለበት፡፡ ምድር በመላእክት ወረራ ነጻ አትወጣም፡፡ እግዚአብሄር ከሰማይ ሆኖ ወደ ምድር ተመለከተ ፣ ሰው ፈለገ፡፡ ይሁን እንጂ ከሰው መካከል ሰው ጠፋ ፤ አንድ ስንኳ፡፡ “ጻድቅ የለም ፣ አንድ ስንኳ ፤ አስተዋይ የለም ፤ እግዚአብሄርን የሚፈልግ የለም ፤ ሁሉ ተሳስተዋል ፣ በአንድነትም የማይጠቅሙ ሆነዋል …” ይላል ሐዋሪው ቅዱስ ጳውሎስ (ሮሜ 3፡10-18) ደግሞም ይላል ፡- “ሁሉ ኃጢአትን ሰርተዋልና የእግዚአብሄርም ክብር ጎድሎኣቸዋል” (ሮሜ 3፡24) ስለሆነም የስላሴ አንዱ አካል የሆነው እግዚአብሄር ወልድ ፣ ቅድመ አለም ቃል ስጋ ሆነ፡፡ በስጋ ምሳሌ አልመጣም ፣ እውነተኛ ስጋ ሆኖ አንጂ፡፡ “የአብርሃምን ዘር ያዘ እንጂ የመላእክትን አይደለም፡፡” (ዕብራውያን 2፡15) ነፃ ልያወጣቸው የመጣው እውነተኛ ሰዎችን ስለሆነ የእነርሱን ማንነት “በስጋና ደም ተካፈለ” (ዕብራውን 2፡15) “በነገር ሁሉም ወንድሞቹን መሰለ” (ዕብራውን 2፡17) ይኼም ፍጽም ሰው ኢየሱስ ተባለ፡፡ ሁለተኛው አዳም ፤ ይህም ሰው በስጋው በኃጢአት ተፈተና (ማቴዎስ 4፡1-11) ኃጢአት ግን አላደረገም፡፡ (ዕብራውያን 4፡14) በስጋው ኃጢአትን ኮነነ፡፡ (ሮሜ 8፡4) እሱ “የአለምን ኃጢአት የሚስወግድ” (ዮሐንስ 1፡29) “ቅዱስና ያለተንኮል ፣ ነውርና ነቀፋ የሌለበት” (ዕብራውያን 7፡26) የእግዚአብሔር በግ ነው፡፡ በመሆኑም እግዚአብሔር “የሁላችንንም ኃጢአት በእርሱ ላይ ማኖር” ይችላል፡፡ ደግሞም አድርጎታል፡፡ ሐዋሪያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይላል “እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው፡፡” (2ቆሮንቶስ 5፡21) ሐዋሪያው ቅዱስ ጴጥሮስም “እርሱም ኃጢአት አላደረገም ፣ ተንኮልም በአፉ አልተገኘበትም፤ ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም ፣ መከራንም ሲቀበል አልዛተም ፤ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ ፤ ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር እርሱ ራሱ በስጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ” …(1ጴጥሮስ 2፡22-24)

 

እንግዲህ ይኸው ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን በጊዜያዊነት የሟች እንስሳ ነፍስ እንደ ኃጢአተኛው የራሱ ነፍስ በምሳሌ ቆጥሮ ለኃጥአተኛው ምህረት ሲያደርግ የነበረው እግዚአብሄር በዚህ የአዲስ ኪዳን ዘመን ደግሞ እውነተኛ ስጋ ለብሶ ፣ ሰውን ሁሉ ወክሎ ኖሮ ፣ በስጋው ኃጢአትን ኮንኖ ፣ በደሙ የኃጢአታችን ስርየት የሚሆን መስዋዕት አውርቦ የድነትን ጉዳይ የጨረሰው የኢየሱስ ክርስቶሰ ስራ ፍፁም የሆነው ፣ ለሰው ሁሉ የሚበቃ የእግዚአብሔር ዘላለማዊ መፍትሔ ነው፡፡ ይኼንን በእምነት ስንቀበለው ያለምንም ተጨማሪ ስራና ልፋት እግዚአብሔር ተቀብሎን እንጸድቃለን፡፡

“በአንድ ሰው በደል ብዙዎች ሞተዋልና ፣ ነገር ግን የእግዚአብሔር ጸጋና በአንድ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ሆነው ስጦታ ከዚያ ይልቅ ለብዙዎቸ በዛ፡፡” (ሮሜ 5፡15) “በአንዱ ሰው አለመታዘዝ ብዙዎች ኃጥአተኞች እንደሆኑ እንዲሁ ደግሞ በአንዱ ሰው መታዘዝ ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ፡፡” (ሮሜ 5፤19) ሁሉ በአዳም ሞቱ ፣ ሁሉ በከርስቶስ ህያዋን ይሆናሉ፡፡ ልክ አዳም ወገብ ውስጥ ሆኖ ከአዳም በኋላ የሚመጡ ሁሉ በለሲቱን እንደበሉ ተቆጥረው ኃጢአተኛ እንደሆኑ በክርስቶስ ማንነት ውስጥ ኢየሱስ በስጋው ያደረገው ጽድቅ (ያለኃጢአት የኖረው ማንነት) ፣ በመስቀል የሞተው ሞት ፣ መቀበሩ ፣ ትንሳኤው በሙሉ በኢየሱስ ክርስቶስ ለሚያምኑ ይቆጠርላቸዋል፡፡ ሕይወቱን የሚመስል ሕይወት ፣ ሞቱን የሚመስል ሞት የተካፈልን ሲሆን ፤ ትንሳኤውንም ተካፍለናል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

x

Check Also

Fikadu Borena Week Four

Related

%d bloggers like this: