Home » Articles » ታላቁ ወንጀል! (Sola Scriptura ስንል…..)

ታላቁ ወንጀል! (Sola Scriptura ስንል…..)

በአሳየኸኝ ለገሰ

 

ሀደን ሮቢንሰን የተባሉ ጸሐፊ፣ ቅዱሱ መጽሐፍ ላይ ከሚፈጸሙ እጅግ የከፉ ወንጀሎች ‹‹ዋነኛው ነው›› ያሉትን ሲያስረዱ እንዲህ ይላሉ፤ “በርካታ ሰባኪያን፣ ለስብከት ወደ ምስባኩ ሲወጡ መጽሐፍ ቅዱስ ይዘው ነው፡፡ ስብከታቸውን ሲጀምሩም ከዛው መጽሐፍ ላይ አንብበው ነው፡፡ የሚሰብኩት ሲፈተሽ ግን (ባነበቡት ክፍል ውስጥ) መጽሐፉ ሊል የፈለገው ሳይሆን፣ ሰባኪዎቹ ሊሉ የፈለጉት ሆኖ ይገኛል፡፡ መጽሐፉን ገልጠው የሚያነቡትም የሕዝቡን ጆሮ ለመሳብ፣ እንደ ‹አፒታይዘር› ሆኖ እንዲያገለግላቸው ብቻ ነው!”….. (ሮቢንሰን ከተናገሩት ጋር የሚስማማ አሳብ ጋሽ ንጉሴ ቡልቻም ያነሳሉ….) “በቤተክርስቲያን መድረክ ላይ ቃሉን ለማስተማር ቆመን፣ እንቅብ ሙሉ የሰው አሳብ እየነዛን የእንቅቡን ክፈፍ በቃሉ ቆዳ ብንለጉም እግዚአብሔር የሚምረን ይመስላችኋል? … ቅዱሱን ቃል ከየጎዳናው ላገኘነው አሳብ መንደርደሪያ… ከየማድጋው ለጨለጥነው ውሃ ማጣፈጫ እንዴት እናደርገዋለን?… ‹‹ቃሉን ስበክ›› ተባልን እንጂ ቃሉን አስታክክ አልተባልንም!”… እንደዚህ ያለውን ድርጊት ‹‹አደገኛ የንግድ ታክቲክ›› ሲሉ ይጠሩትና፣ “የቃሉን እጅ ጠምዝዞ ከሰፈሩ በማፈናቀል በየስርቻው ከመጣል የበለጠ ሌላ ምን ወንጀል ይገኛል?” ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡ … እንደ ባለሙያ አበባ ጎንጓኝ የሚፈልጉትን ብቻ እየነቃቀሱ ቃሉን ከፍጥረቱ ውጪ የሚጥሉትንም በእግዚአብሔር ፊት ከተጠያቂነት እንደማያመልጡ አጽንኦት ሰጥተው ይናገራሉ!… ይህ ቅዱሱ መጽሐፍ ላይ የሚፈጸም ወንጀል ሰባኪያንን ብቻ የሚመለከት አይደለም፡፡ (ጠቢቡ ሰው) ሲ ኤስ ሉዊስ፤ “ብዙዎቻችን ክርስትናን ቀርበን የምናጤነው እውን ክርስትና ምን እንደሚል ለማወቅ ሳይሆን ራሳችን ለምናራምደው አስተሳሰብ የክርስትናን ድጋፍ ፍለጋ ነው!”…ሲል ብዙ ክርስቲያኖች ይህንን ወንጀል ሲፈጽሙ ይገኛሉ ይላል፡፡… .

 

ለመሆኑ እነዚህ ምሁራን ይህ አይነቱን (ቃሉን ከፍላጎቶቻችን ጋር እንዲስማማ አድርጎ የማንበብን ልማድ)፣ “ትልቅ ወንጀል ነው” ብለው የጠሩት ለምንድነው?? ምክንያቱ አንድ ነው፡፡ ቃሉ፣ ከቃሉ አንዳች ነጥብ ተጎምዶ ከሚጣል ወይም ላዩ ላይ ከሚጨመር ‹‹ሰማይና ምድር ቢያልፉ ይቀላል›› ያለው (ቃሉን የሚያከብር) አምላክ ቃል ስለሆነ ነው!! የ16ኛው ክፍለ ዘመን ተሐድሶ አቀንቃኞቹ ማርቲን ሉተር (እና ከሱ በፊትም ሆነ በኋላ የተነሱት) ‹‹መጽሐፍ ቅዱስ ብቸኛ የስልጣን ምንጫችን ነው!” (Sola Scriptura) ያሉትን ማስተጋባት መልካም መሆኑ ቢታመንም፣ ያለ ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ አፈታት (Hermeneutics) መጽሐፉ ባለስልጣን ሊሆን እንደማይችልም መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ተሐድሶአውያኑ፣ የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ውድቀት የመጽሐፍ ቅዱስ ሥነ-አፈታት ችግር ጭምር እንደሆነ ያምኑ ነበር፡፡ ዛሬም “Sola Scriptura!” ስንል ቃሉ በትክክል ይተርጎም ማለታችን ነው! አይደን ቶዘር ሲናገር፣ “ወንጌል ለማዳን የሆነ የእግዚአብሔር ኃይል ነው!(ሮሜ 1፡16) እንግዳ በሆኑ ሰዋዊ አሳቦች ሲሸቀጥና ሲቀየጥ ግን የሚያድን ኃይል መሆኑ ይቀራል!” ብሏል….. መጮህ ያለብን ለዚህ ነው፤ ወንጌሉ በእንግዳ ትምህርቶች ተቀይጦ የማይታወቅና ጉልበት የሌለው ‹‹ልዩ ወንጌል›› ሆኖ እንዳይቀር …. ወንጌል ኃይሉ ሳይደበዝዝ መስራት የሚችለው በታማኝነት የተሰበከ እንደሆነ ብቻ ነውና! ለዚህ ደግሞ ሰባኪው አንድ መሰረታዊ ነገር ማወቅ አለበት፡፡ ቃሉ የእግዚአብሔር መሆኑንና እሱ መልዕክተኛ ብቻ መሆኑን!… መልዕክተኛው መልዕክቱን የማሻሻል፣ የመቀነስ ወይም የመጨመር መብት የለውም!!

 

ስለሆነም ዛሬም “Sola Scriptura” ስንል፤

– ቃሉን ለድህረ-ዘመናዩ ጆሮ እንዲስማማ አስዘምነው የሚያነቡ የስሜት አገልጋዮች ‹‹ውጉዝ ከመአርዮስ!›› ሊባሉ ይገባል ማለታችን ነው…….

– መጽሐፍ ቅዱሳዊውን መለኪያ በእኛ ልክ ያልተሰፋ አሮጌ መመሪያ እንደሆነ በመቁጠር አሽንቀጥረው የጣሉት የ‹‹እንደ ወረደ›› ሰባኪያን ከመድረኩ ሊወርዱ ይገባል ማለታችን ነው…

– የአዕምሯአቸውን አሳብ፣ ቃሉ እንዲያጮህላቸው (ቃሉን እየታከኩ)… የቃሉን ‹‹ልክ›› አጥፍተው በራሳቸው ‹‹ልክ›› የተኩ፤ ነጋዴ ሰብኮ-አደሮች የሕዝበ-ክርስቲያኑን አየር ሊለቁ ይገባል!……እያንዳንዱም አማኝ ‹‹አንሰማችሁም!›› ሊላቸው ይገባል! ማለታችን ነው… . ቃሉ በበላይነት ያላጸደቀውን እንቶ ፈንቶ የሚነዛውን… “ነቢይ” ይሁን “ሐዋሪያ”፣ “መጋቢ” ይሁን “ቄስ”.. (ለምን ‹‹የሰማይ መልዐክ›› አይሆንም…) እምቢኝ! ማለት ጽድቅ እንጂ ኩነኔ ሊሆን አይችልም! ነቅተን የእግዚአብሔርን ሕዝብ ልናነቃ ይገባናል!! የተሰበከውን ሁሉ ያለ ምርመራ (በስመ-እምነት) የሚቀበል ሕዝብ ትልቅ አደጋ የተጋረጠበት መሆኑን እናስተውል! …. ቶዘር፣ “እምነት የተሰበከውን ሁሉ መቀበል አይደለም፡፡ ያገኘውን ሁሉ የሚያምን ሰው፤ የትኛውንም ስብከት ከማያምነው (ከሀዲ) እኩል ከእግዚአብሔር የራቀ ነው!” እንዳለው ነው፡፡ ምርጫው በእጃችን ነው!!… ከገባንበት አረንቋ ፈጥነን መውጣት እንችላለን፡፡ … Sola Scriptura!! የሚለውን ቀደምት ጩኸት እኛም ከተጋራነው፣ ጩኸቱ (የአንድ ሰሞን ሆይ ሆይታ ሆኖ እንዳይቀር) በተግባር እናግዘው! … ይህንንም ወንዝ በማያሻግር ኑፋቄ ቤቱን አጥለቅልቀው… ተራ ልፈፋቸውን ከቃሉ በላይ እንዲከበር ያደረጉትን ‹‹ውሾች›› ከተቀደሰው ስፍራ ገለል በማድረግ ቁርጠኝነታችን እናሳይ!… አምላካችን አዳሻችንና መሐሪያችን… ሕያው ቃሉን አጥርተን እንድናይ አይኖቻችንን እንዲያበራ እምነቴ ጽኑ ነው!! — “እኔ ያዘዝኋችሁን የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ትጠብቃላችሁ እንጂ ባዘዝኋችሁ ቃል ላይ አትጨምሩም፥ ከእርሱም አታጎድሉም!” (ዘዳ. 4፡2)

 

የግርጌ ማስታወሻ

*Haddon W. Robinson: the Develeopment and Delivery of Expository Messages: Biblical Preaching, 26

*ንጉሴቡልቻ፤ መስተአየት፡ ራስታዘብናተሓድሶአውያንመጣጥፎች፣ (አዲስአበባ፣ ሐምሌ 2002 ዓ.ም) 75-76

*ሲ ኤስ ሉዊስ (ተርጓሚ አዲስ አሰፋ)፤ ክርስትናለጠያቂአዕምሮ፤ 81

*በመንፈሳዊ ተሐድሶ ፎረም በጋራ አስተባባሪነት የተዘጋጀ፡ የተሐድሶ ጥር፡ መመርመር-መመለስ-መታደስ፤ 51

*Femi Adeleye, Preachers of a Different Gospel, 61

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

x

Check Also

Fikadu Borena Week Four

Related

%d bloggers like this: