Home » Articles » የእውቀት እና የእውነት መልክ

የእውቀት እና የእውነት መልክ

በአሹቲ ገዛኸኝ

 

ክቡድ በሆነው ምሽት ላይ “ሰውየውን በሕይወት እና በሞት መካከል ደብድበውት ጠፉ” ይለናል፣ የክርስቶስን ምሳሌ እያስታወሰ የሉቃስ ወንጌሉ ፀሐፊ ሉቃስ (ዶ/ር)።

 

መቼም እንደ ካህን በሌሊት የሚነሳ ያለ አይመስለኝም። ይቀድሳል፣ ያስቀድሳልና። እናማ ጎበዙ ካህን ስብከቱን ሰርቶ በሌሊቱ ዘው ዘው እያለ፣ ምናልባትም እኮ ይሄኔ  “እግዚአብሔር ያነሳል” የሚል ስብከቱን በእጁ ይዞ ይሆናል። ወንበዴዎችም የደበደቡት ያ ምስኪን ደሙ እላዩ ላይ እንደተዝረበረበ ለሞት ሲያጣጥር፣ ጎበዙ ሰባኪም የፍቅር ስብከቱን በአግባቡ እንደያዘ ያንን ምስኪን አይቶት እንዳላየ አልፎት ሄደ (ባላየ እንደምነለው በዘመናችን)። እንዴ ያን ግሩም የፍቅር ስብከት ማን ይስበክለት? እናማ መድረኩን ተቆጣጥሮ ከጫፍ እስከ ጫፍ እየተወነጨፈበት ስለ እግዚአብሔር ፍቅር ማውራቱን ቀጠለ። የምዕመኑ እልልታ እና ጭብጨባው ያስተጋባል (ምናልባትም የምእመኑ እልልታ እና ልሳን ከምስኪኑ ጆሮ ደርሷል) ምን እሱ ብቻ ሌዋዊው እንደጠመጠመ ከች፣ እሱም አይቶት እልፍ አለ። እንዴ ማን እጣኑን ያጥን? ማንስ የመቅደሱን ስርዓት ያስጠብቅለት?

እነዚህን የመቅደሱ ስርዓት አገልጋዮች እስኪ ተመልከቱ? በሌሊት የሚነሱ ትጉዎች፣ የወደቀን ለማንሳት እንኳ ጊዜ የሌላቸው ትጉዎች! (“ድንቄም ትጋት”! አሉ እኛ ሴትዮ) ለነገሩ በመንገድ ላይ ያለውን ምስኪን ይህ ካህን (ሌዋዊ) ሲያነሳ ቢቆይ፣ ከአፍላል ከምንቸቱ ማን ይቀምስለታል፣ ቅርጫቱ ውስጥ የምትገባዋን ሳንቲምስ ማን ይቀበልለታል፣ እናማ የኃይማኖቱን ጥምጥም እንደ ተከናነበ ላጥ። እግዚአብሔር በሰው ውድቀት ምክንያት የመቅደሱን ስርዓት ሊለውጥ ይችላል። “ካህናቱ” ግን አይለውጡም። የመቅደሱን ጌታ የሚያዩበት መንፈሳዊ አይን ፈዟልና። የመቅደሱ ጌታ ከወደቁት ጋር ለመጓዝ። እንኳን መቅደሱን ከክብሩ ይወርዳል፣ ወርዷልም! እንዲህ አይነቱ “ካህን” ግን በቀይ ምንጣፍ የተዥጎደጎደ መድረክ ይሰራለት እንጂ እዛውም ይተኛል፣ እዛውም ያስተኛል። እንደ እነ አፍኒን።

 • እግዚአብሔር ፤ እጣኑ የበዛበት ነገር ግን ፍቅር የቀዘቀዘበት መቅደስ አይፈልግም።
  • እግዚአብሔር ትላልቅ ‘ስፒከር’ የቆመበት፣ ድለቃው የጦፈበት ምስኪን ሰዎች የማይስተናገዱበት ኮንፍረንስ የለውም፤ ካህናቶቹ ግን አላቸው። እግዚአብሔር አስደናቂ ሰዎች የበዙለት፣ ሸክም የበዛባቸው የተረሱበት ወንጌል የለውም። አስቀድሞም መቅደስ እግዚአብሔር የሚገለገልበት ብቻ ሳይሆን ፤ የምስኪኖች ድምፅ የሚሰማበት አምላካዊ መድረክ ነበር። መቅደስ ከፈረሰም አምላክ እና ሰው ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት እንዲግባቡ መንፈሱን ለሰዎች በማደል ነው።
  • አምላክን ያለ እውቀት ማገልገል ብዙ ነገር ማበላሸት ነው። ከዚያ በላይ ያወቁትን ያለመኖር ግን ትልቅ በደል ነው።
  • እውቀት መቅደስ ውስጥ በአርባ ክንድ የሚያስር ገመድ ሳይሆን ከመቅደስም ወቶ ለሰዎች ቁስል መፍትሄ የሚሰጥ ነው።
  ጌታም የእውቀቱን ቃል ሲተረትር እንዲህ አለ “የነቢዩንም የኢሳይያስን መጽሐፍ ሰጡት፥ መጽሐፉንም በተረተረ ጊዜ። የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፥ ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና፤ ለታሰሩትም መፈታትን ለዕውሮችም ማየትን እሰብክ ዘንድ፥ የተጠቁትንም ነጻ አወጣ ዘንድ የተወደደችውንም የጌታን ዓመት እሰብክ
  ዘንድ ልኮኛል ተብሎ የተጻፈበትን ስፍራ አገኘ።” (ሉቃ 4 : 17-19) አይገርምም!?

በዚው ቃል መሰረት መንፈስ ከበዛልን ታች ያሉትን፣ የተጠቁትን ለማገልገል እንጂ ለእውቅና አይደለም (ቢታወቁም ችላ ማለት ነው ያዘናጋልና)።
እኛ ግን የመቅደስም መቅደሳዊ የሆንን ይመስለኛል።
• እኛማ መዝሙራችንን እንስራ እንጂ ጌታ ስለሚጨነቅላቸው ምን አስጨነቀን?
• እኛማ ብዕራችን ጦሙን ላያድር እንሞንጭር እንጂ ወንጌሉን በእውነት ለማድረስ መች እናስብና?
• እኛማ ባማረ ልብስ ተሽቆጥቁጠን መድረክ አጣበን እንቁም እንጂ ቁስለኞችን ማከም ለምን ያስፈልገንና? ሊያውም ቁስለኛን ያነሳንበት የደሙ ምልክት የሌለን ንፁህ ጥምጥም ለባሾች አይደለንም ወይ?
• እኛማ በጌታ ነፃ የወጣን እንጂ የሌላው እንባ የማይገባን የጌታ የዝላይ አምላኪዎች አይደለን? • ነገሩስ የራቀውን ማንሳት ይቅርና እርስ በርስ መች እንስማማና?
• ለራሳችን የተጠመቅን…የራስ ትጉዎች አይደለን ወይ?
ይልቅስ ሁላችን ለእውነቱ ቃል በጊዜ እንንቃ!!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

x

Check Also

Fikadu Borena Week Four

Related

%d bloggers like this: